የአባይ ውሃ ጦርነት ነገር ከግብጽ አንደምታው እና የሽሚያ/ፉክክር ድርድር ስልት

ዘሪሁን አበበ ይግዛው

ዋናው ጉዳይ-እንደ መንደርደሪያ

ሰሞኑን የዓለም መገናኛ ብዙሃንን ጆሮ ቀጥ አድርጎ የያዘ አንድ ታላቅ ጉዳይ ቢኖር የአባይ ውሃ ጉዳይ ነው፡፡ ለረጅም ዘመን በአባይ ውሃ የመጣ ከእኔ በላይ ላሳር ነው ትል የነበረችው ግብጽ በግንቦት 14 ቀን 2010 እኤአ (ሁሉም ዓመተ ምህረቶች እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ናቸው) አምስት የናይል ተጋሪ የራጌ ተፋሰስ ሀገራት (ኢትዮጵያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ሩዋንዳ ) በሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ ኬንያ እንዲሁም በየካቲት 2011 ቡሩንዲ የተፈረመው የናይል ውሃ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ መፈረም ምክንያት የበላይነቷን ለማስጠበቅ ያላደረገችው ነገር አልነበረም፡፡ ግብጽ ይህን ስምምነት የተቃወመችው በአንድ እና አንድ ምክንያ ነው፡፡ ይኸውም ስምምነቱ ሁሉም የአባይ ተፋሰስ ሀገራት በፍትሐዊ አና ምክንያታዊ መንገድ በሌሎች ተጋሪ ሀገራት ላይ የጎላ ጉዳት ላለማደረስ በመጣር መጠቀምን ስለሚደነግግ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ስምምነቱ ሁሉም ሀገራት በናይል ወንዝ ላይ እኩል ባለቤትነት እና እኩል ድምጽ እንዳለቸው ያውጃል፡፡ ማንም ሀገር ፈቃጅም ከልካይም ሊሆን አይችልምና፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ስምምነቱ የሁሉንም ሀገራት የውሃ ዋስትና/ደህንነት ያውጃል፡፡ አሁን የትብብር ስምምነት ማዕቀፉ በፈራሚዎቹ መካከል ቀያጅ ህግ ለመሆን የሚፈልገውን የስድስት ሀገራ ፊርማ አግኝቷል፡፡ ደቡብ ሱዳን እና ኮንጎም እንደሚፈርሙ ይታመናል፡፡ ይህ ስምምነት ጸድቆ ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲሁም የተባበሩት መንግስታት ሲገባ የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን ይቋቋማል፡፡ ነገር ግን ይህን ስምምነት ሁለት የግርጌ ሀገራት በተለይ ግብጽ ሊዋጥላቸው አልቻለም፡፡ ይህም የሆነው ግብጽ አለኝ የምትለው እና ለራሷ ማንም ሳያውቅ እና ሳያረጋግጥ ከሱዳን ጋር በፈረመችው ስምምነት የተሰጠኝ በምትለው የውሃ ኮታ ይከበርልኝ ጥያቄ እና ፍላጎት ነው፡፡ ይህ ስምምነት ለላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የለም፡፡ አያውቁትምም፡፡ አንድም አልተደራደሩበት አልተማከሩበትም፡፡ ሁለትም አመልክተው አልተቀላቀሉም፡፡ ሶስትም ከመጀመሪያ ጀምሮ በተለይ ኢትዮጵያ በኋላም በነጻነት አፍሪካውያን ወንድሞች ከነጭ አባይ ሀገራት እንደሚቃወሙት እና እንደማይመለከታቸው አቋማቸውን በግልጽ አሳውቀዋል፡፡ ይህም ተፋሰሱ በሀገራቱ የብሔራዊ ጥያቄ አቋም መሰረት ተፋሰሱን የግራጌ እና የራስጌ ተብሎ እንዲከፈል አድርጎታል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገራት ሉአላዊ በሆነ ይዞታቸው ያለን ማንኛውንም የተፈጥሮ ሀበት የመጠቀም መብት ስላላቸው የራስጌ ሀገራት አንዳንድ የውሃ ልማት ስራዎችን መስራት ቀጠሉ፡፡ ለምሳሌ ያክል ኢትዮጵያ በተከዜ እና ጣና-በለስ፣ ኡጋንዳ በቡጃጋሊ ግድብ፡፡ይህ የራስጌ ተፋሰስ ሀገራት የውሃ ልማት ስራ ከ ግብጽ የአዲሱ ሸለቆ ልማት ፕሮጀክት-ቶሽካ፣ አል-ሰላም እና የደቡብ-ምዕራብ በረሐ ልማት እንዲሁም ሱዳን የሜሮዊ ግድብ፣ የሮዛሬስ ግድብን የማስረዘም፣ የአትበራና ሰቲት ፕሮጅክቶች እንዲሁም አሁን ደግሞ የካጅባር ግድብ ስራ ጋር ሲነጻጸር ምንም ማለት አይደለም፡፡ የሆኖ ሆኖ ኢትዮጵያ በሚያዝያ 2 ቀን 2011 በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒሰትር አቶ መለስ ዜናዊ አብሳሪነት የመሰረት ድንጋይ የተጣለለትን የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ መገንባት ጀመረች፡፡ እንሆ 21 በመቶ ተጠናቀቆ የዋና ግድብ ግንባታው ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ነገር ግን ሁለት ሁነቶችን ተከትሎ ከግብጽ የጦርነት ታምቡር ድለቃ ከተጀመረ ሰነባበተ፡፡ አንደኛ በግንቦት 28 ቀን 2013 የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተወሰኑ ሜትሮች የማቀየስ ስራ በተሳካ በሁኔታ መጠናቀቁ ነው፡፡ ይህ ምንም አይነት ውሃ የመቀነስም ሆነ ምንም ተጽእኖ በውሃ ፍሰት ላይ ባይኖረውም የግብጽ መገናኛ ብዙሃን ወንዙ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንደተቄሰ አድርገው ማራገባቸው በውስጥ ችግር ለምትታመሰው ግብጽ አንድ ሌላ ችግር ነበር፡፡ ችግር የሆነው የመገናኛ ብዙሃኑ አዘጋገብ እንጅ ሌላ አይደለም፡፡ ሁለተኛ ኢትዮጵያ ከመልካም ጉርብትና እና በሁሉም ተፋሰስ ሀገራት ስለግድቡ እና ስለ ኢትዮጵያ ልማት እምነትን ለመፍጠር በማሰብ የተቋቋመው ከግብጽ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ሁለት ሁለት እንዲሁም አራት በሀራቱ የተመረቱ ዓለምአቀፍ ባለሙያዎችን የያዘ የዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድን የመጨረሻ ሪፖርት ማቅረቡ ነው፡፡ እንደ ሪፖርቱ ከሆነ የሚገነባው ግድብ ለግርጌ ሀገራት የጎላ ጉዳት እንደሌለው ይልቁንም ጥቅም እንደሚሰጥ ደነገገ፡፡ ከዚህም ጋር አያይዞ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን ለመጨመር እንዲሁም ያልጣዩ ጉዳቶች ድንገት ካሉ ተጨማሪ ጥናት ቢጠና መልካም እንደሆነ መከረ፡፡ ይህንም ተከትሎ ሱዳን እና ኢትዮጵያ የባለሙያዎቹን ሪፖርት ተቀበሉ፡፡ እየመረመሩትም ይገኛል፡፡ ሱዳን ከዚህም በማለፍ የግድቡ መሳካት ለሱዳን መቀደስ እንደሆነ የባለሙያም ድጋፍ እንደምታደርግ ገለጸች፡፡ ነገር ግን የግብጹ መሪ ሞሀመድ ሞርሲ የጅብ ችኩል እንዲሉ ኢትዮጵያ ያጠናቸው ጥናት በቂ አይደለም ወዘተ ግድቡ ግብጽን ይጎዳ ወደሚል መግለጫም ወቀሳም አመሩ፡፡ ይህ የመገናኛ ብዙሃኑ የጠዛባ ሀተታ ጋር ተያይዞ የአባይ/ናይል ተፋሰስ የውሃ ጦርነት ዋዜማ ላይ እንዳለ አስመሰለው፡፡

ሁለት የከፉ ነገሮች ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ ከግብጽ ተስተውለዋል፡፡ አንድም ግብጽ ፖለቲከኞች በድንገት በቀጥታ በቴሌቪዥን በተላለፈ ናይልን እና የኢትዮያን ግድብ አጀንዳ ባደረገ “ውይይት” ኢትዮጵያን የማተራመስ እቅድ፣ ግድቡ ላይ ዘመቻ የማካሄድ እነዲሁም ኢትዮጵያን በዓለምአቀፍ መድረክ በተለይ በአረብ ሀገራት ዘንድ የማስቀረፍ እና የማሸማቀቅ ስልት እንከተል ብለው አወጁ፡፡ ዓለም ይህን አየ፡፡ ግብጽን እየመሩ ያሉት እነማን እንደሆኑም ተስተዋለ፡፡ የውይይቱ አካል የነበሩት የሐገሪቱ ፕሬዝዳንትም አንዲት ሉአላዊት ሀገራት ላይ የተደረገው ዛቻ ምንም አልመሰለቻውም፡፡ ይልቁንም በውጭ ጉዳይ አማካሪያቸው ሀዳድ አማካኝነት ለስካይ ኒውስ መንግስት አይደለም ይህን ያለው ፖለቲከኞች ናቸው ያሉት፡፡ የፈለጉትንም መናገር ይችላሉ ብለው አረፉት፡፡ በመሐል ግን ከእብድ መሐል የተገኘ ጥሩ እንዲሉ ሞሀመድ አልበራዳይ የኢትዮጵያ እና የሱዳንን ህዝብ ይቅርታ ጠየቁ ባተሳተፉበት ስለ ሀገራቸው ሲሉ፡፡ የሆነ ሆኖ ለዚህ ሁሉ የጦርነት ታምቡር የኢትዮጵያ መልስ አንድ ነበር፡፡ የተነገረው ነገር ሁሉ የታሰበም ካለ “የቀን ቅዠት ነው” የሚል፡፡ ሁለተኛው እና አሳፋሪው ነገር የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት በትናነትናው ዕለት ሰኞ 11 ሰኔ 2013 እስላማዊ ፓርቲዎች (የራሳቸውን ጨምሮ) በጠሩት ኮንፈረንስ ላይ እርስበርሱ የሚጋጭ ነገር ግን ጦርነት ናፋቂ የሆነ ንግግርን አደረጉ፡፡ ወደዝርዝሩ አንገባም፡፡ የተባለው ተብሏል፡፡ ነገር ዋናው ጥያቄ ይህ እየጠደጋገመ ያለ የቶርነት ታምቡር ዋና ዓላማው ምንድን ነው የሚል ይሆናል፡፡ ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት ግን የውሃ ጦርነት ሊነሳ ይችላል ወይ የሚለውን እንደሚከተለው እንዳስሳለን፡፡

ዕውን የውሃ ጦርነት በአባይ ይኖራልን?

እስካሁን ድረስ በውሃ የተደረገ ጦርነት የለም አልተደረግም ብለው የሚከራከሩ የውሃ ፖለቲካ አጥኚወች አሉ፡፡ ሆኖም ግን ውሃ በሀገራት መካከል በተደረጉ ጦርነቶች ዋና መነሻ እና ምክንያት ባይሆኑም በትንሹ የግጭት አቀጣጣይ እና መሳሪያ ሆኗል ብለው ያምናሉ፡፡ የሆኖ ሆኖ የዚህ ጽሁፍ ጸኃፊ የውሃ አካልን ለመቆጣጠር የተደረገ ጦርነት እንደነበረ ያምናል፡፡ ይህም በ19ኛው ክፈለ ዘመን በኢትዮያ እና በግብጽ መካከል የተደረጉት አስራ ስድስት ጦርነቶች የምንም ሳይኑ የውሃ ናቸው፡፡ በሁሉም ጦርነቶች ግብጽ ሽንፈትን አስተናግዳ ተመልሳለች፡፡ አንዳድ አጥኚዎች በተፋሰሱ እየቸመረ ያለውን ህዝብ፣ በዓለም አካባቢያዊ ሙቀት መጨመር እየጠጎሳቀለ ያለውን የውሃ መጠን እንዲሁም በሀገራቱ መካከል ያለውን የፖለቲካ እና አጠቃላይ እሳቤ ልዩነት፣ በታሪክ የነበረ ቁርሾ በመመልከት የናይል ተፋሰስ ከየትኛው ደንበር ተሸጋሪ ወንዝ የበለጠ ለጦርነት ተጋላጭ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን ይህን የሚሉት አካላት ከግብጽ እና ግብጻውያን ፖለቲከኞች በሚሰሙት ንግግሮች እና አስተያየቶች የተጠለፉ እንደሆነ ማረዳት ከባድ አይደለም፡፡ ምንጊዜም ቢሆን ይኖራል የሚሉትን የውሃ ጦርነት ለማስረዳት እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት የሶስት ግብጻውያንን ንግግር  ነው፡፡

በ197ዎቹ መጨረሻ ከእስራኤል ጋር ስምምንት ያደረጉት የግብጹ መሪ ሞሀመድ አንዋር አል ሳዳት “ከአሁን በኋላ ግብጽን ወደ ጦርነት የሚወስዳት ነገር ቢኖር ውሃ ብቻ ነው” ማለታቸው በውሃ ጦርነት አቀንቃኞች ዘንድ የተመረጠ ማጣቀሻ ነው፡፡ ሌሎቹ ማጣቀሻ ግብጻውያን ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ እና እስማኤል ሰርጋልዲን ናቸው፡፡ በ1988 ዓ.ም. የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩ ጊዜ የኋላው የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸኃፊ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊ “በክፈለ ዓለማችን ቀጥሎ የመደረገው ጦርነት በውሃ ምክንያት እንጅ በፖለቲካ አይደልም”  ማለታቸው ነው፡፡ እንዲሁም በ1995 የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዝደንት የነበሩት ግብጻዊው ኢስማዔል ሰርጋልዲንም በፈንታቸው “ባለንበት ክፍለ ዘመን ብዙዎቹ ጦርነቶች የተደረጉት በነዳጅ ዘይት ምክንያት ነበር፡፡ ነገር ግን የሚቀጥለው ክፍለ ዘመን ጦርነት በውሃ ይሆናል” ማለታቸው የብዙ ፊደላውያን ማጣቀሻ ነው ስለ ውሃ ጦርነት፡፡ እንግዲህ ግብጻውያኑ በዚህ ዓይነት ስልት የውሃ ጦርነት ተፈርቶ ሳይበላ እንዲታደር ነበር ሙከራቸው በአባይ ተፋሰስ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ቃላዊ/አፋዊ የሆነ ነገር እንዳለ ሆኖ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እውን የአባይ ውሃ ጦርነት ይኖራልን?

የአባይ ውሃ ጦርነት ይኖራል ብሎ የሚያስደፍር አንዳችም ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ አጆቿን አጣጥፋ ጥቀመጥ ማለት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በውሃ ምክንያት ጦርነት የማስነሳትም ሆነ የመግጠም ፍላጎት የላትም፡፡ ግብጽም ከጦርነት አተርፋለሁ የሚል እምነት አላት ብዮ አላምንም፡፡ የሆነ ሆኖ የረጅም ጊዜ ጠባሳው ለእነሱው ስለሚከፋ፡፡ የሆነ ሆኖ ጦርነት ይሁን ካለች ልትል እምትችለው ግብጽ ናት፡፡ ይህንም በተደጋጋሚ ፖለቲከኞቿ ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው ማታቸው ይህን ያሳያል፡፡ በመቀጠልም ፕሬዝዳንት ሞርሲ ስለ ውሃ ሲናገሩ “ደማችን የውሃው አማራጭ ነው” ማለታቸው ቃላዊው ንግግራቸው አስቆጭ ቢሆንም በኢትዮጵያ በኩል “ውሃ ከደም ይወፈራል” የሚል ንግግር እንዳለ ያጡታል ብዮ አላምንም፡፡ ይሁን እና የግብጽ ፖለቲከኞች ከቃላዊነት ፉከራ እና የጦርነት ቀረርቶ ዘለው ወደ ተግባራዊ ጦርነት ያመራሉ ብዮ አላምንም፡፡ ይህም መሰረታዊ ምክንያቱ የግብጽ ብሔራዊ ጥቅም በአባይ ላይ በጦርነት የሚጠበቅ እና የሚከበር ስላልሆነ ነው፡፡ ይህ ማለት ግብጽ ጦርነት የማትጀምረው ለኢትዮጵያ ወይም ለሌላ አካል ብላ ሳይሆን ለራሷ ብሔራዊ ጥቅም ስትል ብቻ እና ብቻ ነው፡፡

አንደኛ ግብጽ የአባይን ውሃ በጦርነት ማስገበር አትችልም፡፡ በአፍሪካ በሀብት ብዛት ሁለተኛ የሆነችውን እና እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊቷ የተደራጀ እና በጠንካራ አቋም ላይ ያለችን ኢትዮጵያን መውረር ዋጋ እንደሚያስከፍል ታውቀዋለች፡፡ ወጋው ተከፍሎም ውሃው ያለመቋረጥ እንዲፈስ ማድረግ አይቻልም፡፡ ምክንያም አቶ መለስ ዜናው ያሉትን ልዋስ እና “ግብጽ ኢትዮጵያ አባይን እምዳትጠቀም ለማድረግ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ መያዝ ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ደግሞ ማንም አላደረገውም፡፡” ሊደርገውም አይችልም፡፡ እንኳን ግብጽ ኢትዮጵያን አሜሪካም በአቅምም በምንም የምታንሰውን አፍጋኒስታንን መቆጣጠር አልቻችም ነበር በቅጡ፡፡ ሁለተኛ ግብጽ ካደረገች ልታደርግ የምትችለው የግድቡን ቦታ በአየር መደብደብ ነው፡፡ ያስ ያዋጣል ወይ ብንል አያዋጣም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ የኢትዮጵያ እርምጃም ተመሳሳይ ነው የሚሆነው፡፡ ይህም ማለት ከአስዋን ግድብ ግርጌ ተቀምጦ እንዲህ ዓይነት እቃ-እቃ ጨዋታ ውስጥ ይገባሉ ብዮ አላስብም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚነሳው ሃሳብ የተገለጸው የረጅም ጊዜ ስልታዊ ኪሳራ ነው የሚሆነው ልግብጽ፡፡ ዞሮ ዞሮ የውሃው ምንጭ ኢትዮጵያ ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ግልጽ ነው፡፡ ወደ ዝርዝሩ አልገባም፡፡ ሶስተኛው ግብጽ በአባይ የተነሳ የማትገባበት ወደ ጦርነት የማትገባው ለአማራጭ የውሃ አቅርቦት የሚወጣው ወጪ እና ለጦርነት የሚወጣው ወጪ ትርፍ እና ኪሰራ ስሌት ሁለተኛውን ስለሚያገነው ነው፡፡ ግብጽ በዓለም ካሉ ሀገራት በከርሰምድር/ground water እጅግ ሐብታ ከሚባሉት ሀገራት አንዷ ናት፡፡ እንዲሁም ደግሞ ዙሪያዋን በቀይ ባህር እና በሜዲትራኒያን ባህር የተከበበች ሀገር ናት ግብጽ፡፡ ይህ ማለት ለጦርነት የምታውለውን ገንዘብ የከርሰምድር ውሃ ብታወጣበት ወይም ደግሞ የባህር ውሃ ብታጣራበት ይቀላታል፡፡ በ1990ዎቹ የግብጽ ውሃ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ሞሐመድ አበድል ሀዲ ራዲ ለሳንታዊው አል-አህራም ጋዜጣ በ1995 “የሰውም ሆነ የገንዘብ ወጭው ሲታይ በውሃ ምክንያት ከሚደረግ ጦርነት ይልቅ ምንም ብዙ ገንዘብ ቢጠይቅ የባህር ውሃን ከጨው የመለየት ስራ/desalination ወጭ ምንም ማለት አይደለም” ብለው ነበር፡፡ የአሁኗ ግብጽ ለጺከኞችም ይህን ያጡታል የሚል እምነት የለኝም፡፡ አራተኛው ምክንያት ጦርነት እንዲሁ ዘው ብለው የሚገቡበት ነገር አይደለም፡፡ የአፍሪካ ቀንድ እና ሰሜን አፍሪካ ሲነካካ የሚነካኩ ብዙ ጉዳይ ያላቸው አካላት አሉ ይህ እንዳይሆን የሚፈልጉም የሚጥሩም፡፡ አምስተኛ የግብጽ ውሃ ሚኒስትር ሞሀመድ አል ዲን እንዳሉት ግብጽ ጉዳዩን ውደ ዓለመአቀፍ ገላጋይ ኮሚቴ ልትወስደው ትችላለች፡፡ ሶስተኛ ወገን ባንድም በሌላም መልኩ መግባቱ ስለማይቀር፡፡ ስለዚህ የውሃ ጦርነት በአባይ ላይ ሊኖር አይችልም፡፡ እድሉ እጅግ በጣም ጠባብ ነው፡፡ ሌላው ቢቀር ለውክልና ጦርነት እንኳን ቦታው የለም (በሌላ እትም እንመለስበታለን)፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ ነገር ካለ የእነ ፕሬዝዳን ሞሀመድ ሞርሲ ደም ማሽተት እና የጦርነት ታምቡር መደለቅ ምክንያ ምንድን ነው? ይህን ከመመለሳችን በፊት አንዲት አጭር ጥያቄን እንጠይቅ እና እንመልስ፡፡

ግብጽ ለምን የኢትዮጵያን አባይን ማልማት ትቃወማለች?

በአባይ ላይ የጠደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሰራ ማንኛውም ግድብ እና ሰው ሰራሽ ሐይቅ ለግርጌ ሀገራት ያለው ጥቅም እጅጉን ከፍ ያለ ነው፡፡ ግብጻውያኑ ይህንን ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በማያያዝ ጉዳት ካለ የሚደርሰው ጉዳት እጅጉን ኢምንት ነው፡፡ ይህንም ጠንቅቀው ያውቃሉ ግብጻውያን፡፡ ነገር ግን ግብጽ በኢትዮጵያ አባይ ላይ በሚሰሩ የውሃ ፕሮጀክቶች ላይ አይኗ ደም የሚለብሰው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ አንደኛው የኢትዮያ እነዚህን ግድቦች መስራት ፖለቲካዊ መልዕክት ስላለው ነው፡፡ ለግብጽ ከአሁን በኋላ የአባይ ወንዝ ጉዳይ አዛዥ ናዛዥ ነኝ መላት እንደማትችል፣ በአባይ ወንዝ ማንም የበላይ ወይም የበታች ሀገር እንደሌለ፣ ሁሉም ሀገራት እኩል እንደሆኑ ስለሚናር ነው፡፡ ሁለተኛው አበይት ጉዳይ ግብጽ አለመታደል ሆኖ ፍርሀተ-ኢትዮጵያ/Ethiophbia ያለባት ሀገር ናት፡፡ ይህንም Hydropolitics of Eastern Nile Basin: the Nexus between Water Shaing and Benefit Sharing Arrangements  በሚል ጥናታዊ ስራ ለማተት ተሞክሯል፡፡ ስለዚህ ጨዋታው የእምነት ማጣት ወይም የጥርጥር ነው፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ግብጽን ለመጉዳት ተኝታ አታውቅም ከማለት የፍርሀት ምንጭ የተቀዳ ነው፡፡ ከዚሁ ፍርሀተ-ኢትዮጵያ ጋር የሚያያዘው ጉዳይ በግብጻውያን ዘንድ ተንሰራፍቶ የሚታየው የግንዛቤ ችግር ነው፡፡ ይህም በእያንዳነንዱ የኢትዮያ የውሃ እንቅስቃሴ ውስጥ እስራኤልን እና አሜሪካን እጃቸው እንዳለ አድርጎ መሳል ዋና ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለሆነም ዋናው የግብጽ ትኩረት እና የግድብ ተቃውሞ ከሱዳን ጥቂት አስር ኪሎ ሜትሮች የሚርቀው ግድብ ውሃውን የሚስር እና የሚቀንስ ሆኖ ሳይሆን የፖለቲካ እና ስነልቦና ጉዳይ መሆኑ ነው፡፡

 የግብጽ ውሃ ጦርነት ታምቡር ዓለማዎች

ፕሬዝዳንት ሞርሲ የሚመሩት መንግስት የጦርነት ከበሮውን የሚደልቁት እንደ እኔ እምነት በሁለት አበይት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛው ውስጣዊ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ራሱ የአባይ ውሃ ፖለቲካ ነው፡፡

ውስጣዊውን ችግር በአባይ ማስተንፈስ

እንደሚታወቀው ከቀድሞው አምባገነን ሆስኒ ሙባርክ በአረቡ ዓለም በተቀጣጠለው የመንገስት ለውጥ ምክንያት ከቤተ-መንግስት ከወጡ ወዲህ ግብጽ ራስምታቷ ጨምሯል፡፡ ለረጅም ጊዜ ከፖለቲካው መድረክ ውጭ የነበሩት አክራሪ እስላማዊ ቡድኖች የሀገሪቱን ፖለቲካዊ ምህዳር እንዳሻቸው እና በፈለጉት አቅጣጫ ለመዘወር መከጀላቸው አንድም ከሀገራቸው ሊበራሎች እና በሐይመኞት እና መንግስት መለያየት ከሚያኑ ሁለትም ከዓለምአቀፉ አካል-በተለይ ከምዕራውያን ጋር አላትሟቸዋል፡፡ የሙስሊም ወንደማማቾች ህብረትም ሆነ ወደ 11 የሚጠጉት ሳላፊስቶቹን ጨምሮ እስላማዊ ቡድኖቹ ሀገሪቱን ከነጻ ሊበራልነት ወደ እስላማዊ ቅኝት የመውሰድ አዝማሚያም ለክርስቲያኖች የሚዋጥ አይደለም፡፡ በዚህ መሐል እንግዲህ ራሳቸው ፕሬዝዳንት ሞረሲም እንደ ፈርኦን መሆን ቃጥቷቸው ስለነበረ ሀገሪቱ ከመቼውም ጊዜ ተከፋፍላለች በውስጥ ፖለቲካ፡፡ ለዛም ነው በሰኔ 30 ቀን ፕሬዝዳንት ሞርሲን ከስልጣን ለማወረድ ቆርጠው የተነሱ አማጮች/rebels በሚል ስያሜ በመንቀሳቀስ የፕሬዝዳቱን ስልጣን እየተገዳደሩ ያሉት፡፡ ዓለማቸውም ወደ 15 ሚሊዮን ድምጽ በማሰባሰብ ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን ማባረር ነው፡፡ ስለሆነም ይህን የተቃዎሞ ማዕበል የሚያስተነፍሱበት አንዳች ጉዳይ መጣላቸው ልፐሬዝዳንቱ፡፡ የአባይ ጉዳይ፡፡ ይህንም በተመለከተ ተቃዋሚ መሪዎቹ-ራሳቸውን አማጭ  ብለው የሰየሙት አስታባሪዎቹም ፕሬዝዳንቱን የሀገሪቱን የውስጥ ችግር ለማተንፈስ የአባይን ውሃ ፖለቲካ እየተጠቀሙ ነው ሲሉ የከሰሷቸው፡፡ ይህንም ሲያስረግጡ በሰኞው ንግግራቸው “ልዩነታችንን አስወግደን አንድ መሆን አለብን” ማለታቸው እና ባፈው ሳምንት በፕሬዝዳቱ ቢሮ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት በሚል በጠሩት እና እጅግ አሳፋሪ በነበረው ድራማ ላይ ዋና ዋና ተቃዋሚዎች ሞሐመድ አል-ባራዳይ፣ ሀመዳን ሳባሂ እንዲሁም አመር ሙሳ አለመገኘታቸው ነው፡፡ ስለሆነም ይህን ልዩነት ለማክሸፍ ፕሬዝዳንቱ የአባይን ጉዳይ የአብርሐም/ኢብራሒም በግ አድርገው ማቅረባቸው ነው፡፡ ግን ይህ ነገር ለግብጽ አጠቃላይ ብሔራዊ ጥቅም ያዋጣል ወይ… መልሱ አይደለም ነው.. ዓለም እየተመለከተ እየታዘበም ነ ውና

የጦርነት ታምቡር እንደ የሽሚያ/ፉክክር ድርድር ስልት

በቀዳሚነት የአባይን ውሃ የውስጥ ፖለቲካን ለማተንፈስ እየተጠቀሙበት ቢሆንም ከፍ ያለ ዓላማው ግን ይህ የጦርነት ታምቡር አካሄድ የኃይል-ተኮር ዲፕሎማሲ / coercive diplomacy የድርድር አካል መሆኑን ይህ ጸኃፊ ያምናል፡፡ ከመግቢያችን የጠቀስነው የናይል የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ የዚህ የግብጽ ፖለቲከኞች ቀርረቶ ዋና አካል ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የራስጌ ሀገራት ግብጽ እና ሱዳን ፈረሙም አልፈረሙም የናይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽንን እንሚያቋቁሙ ስምምነቱን በፈረም አሳይተዋል፡፡ ግብጽ ደግሞ ይህ ነገር አልተዋጠላትም፡፡ ምክንያቱም የ1959 ስምምነት በራስጌ ሀገራት ዘንድ ተቀባይነት የለለው መሆኑን ስምምነቱ ስለሚደነግግ፡፡ ስለዚህ ግብጽ አሁን ኢትዮጵያ እየሰራች ያለችውን የታላቁ ህዳ ግድብን ለዚህ ስምምነት ማፍረሻ ዋነ መሳሪያ ለማድረግ ነው ትረቷ፡፡ ላላፉት ተከታታይ ቀናት ጆሮ እስኪበሳ ድረስ ግብጻውያን ፖለቲከኞች ሲደሰኩሩት የነበሩት ቃላት ይህ የሚሰራ ግድብ “የውሃ ደህንነታችን እና የውሃ ኮታችንን” በፍጹም መንካት የለበትም የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ኮታ የሚባል ነገር ከራስጌ ሀገራት ዘንድ አይታወቅም፡፡ ስለሆነም ግብጽ ይህ ነገር በሀገራቱ ዘንድ በተለይ 86 በመቶ ውሃ በምታበረክተው ኢትዮጵያ ተቀባይነት እንዲያገኝ ትፈልጋለች፡፡ ይህን ለማሳካትም ወደ ድርድር ከመግባቱ በፊት ነገሩን ማጮህ አንድ ስልት ነው፡፡

በአንድ ጉዳይ ድርድር ሲካሔድ ሀገራት የራሳቸውን ፍላጎት በሌሎች ላይ ለመጫን ወይም የሌችን ሀገራት ጥቅም ለራሳቸው ለማዋል እጅግ በጣም ጫፍ ላይ ይቆማሉ፡፡ የመደራደሪያ መነሻቸውም ይህ ነገር የእኛ ቀይ መብራት ነው የሚል ሀተታ ይቀናቸዋል፡፡ በሰኔ 2 ቀን 2013 የግብጹ ፕሬዝዳንት አማካሪ  ያሉትን ማስታወስ ለዚሁ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ አማካሪ እንዳሉት “ኢትዮጵያ የግድቡን ስራ ማቆም አለባት ካሆነ ግን ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው” የሚል ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በኩል የጠሰጠው መልስም ግልጽ እና አጪር ነበር፡፡ “የግድቡን ግንባታ ማቆም የማይታብ ነው” የሚል፡፡ ግብጽ ግድብ ግንባታው እንደማይቆም ታውቀዋለች ነገር ግን የችግሩን አሳሳቢነት ለማግነን እና ለማጦዝ እንዲህ ዓይነት ቃላዊ የጦርነት ቀረርቶዎችን ማስተጋባት እንደ አንድ ስልት መጠቀሟ ነው፡፡

አሁን ባለው የአባይ ውሃ ፖለቲካ እና ከግድቡ ጋር በተያየዘ ስለሚነሳው ግርግር ሁለት ነገሮችን እናስተውላለን፡፡ ይህም አንደኛው ግብጽ የፉክክር እና ሽሚያ ዓላማን ያማከለ ስልት ስትከተል በአንጻሩ ኢትዮጵያ የትብብርን ዓላማው ያደረገ ስልት ትከተላለች፡፡ ከግርጌ ተፋሰስ ሀገራት ከወትሮው በተለየ ሱዳን ኢትዮጵይን በመቀላቀል የትብብሩን ስልት መርጣለች ምክንያም ግድቡ የሚሰጠውን ጥቅም ስለምታውቅ፡፡ የፉክክር ወይም የሽሚያ ድርድር አካሄድ በመሰረቱ ከሌላኛው ተደራደሪ የበለጠ ለመውሰድ የሚደረግ ጥረት ስለሆነ የሚጠቀማቸው ዓላማ ማሳኪያ ስልቶችም በዚያው የጦዙ ናቸው፡፡ ይህም ሌላኛውን ተደራዳሪ የማሸማቀቅ፣ የማንኳሰስ፣ አመጣብሃለሁ የማለት፣ የዛቻ ወዘተ ንዑስ ስልቶችን ይጠቀማል፡፡ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ይህ ነገር ለምሳሌ የሰራዊት ሰልፍን እንዲሁም የተሟሟቀ ወታደራ ልምምድን ይጨምራል፡፡ ሰሜን ኮሪያን እና የባለፈውን የሰሜን ኮርያን ግርግር አስታውሱ፡፡ (ለግንዛቤ ያክል ግብጽም ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ብቅርቡ ወታደራዊ ልምምድ ትጀምራች፡፡)፡፡

ድርድርን ወደ ፉክክር/ሽሚያ ዓላማነት የሚቀይሩ ሀገራት በዙ ጊዜ ስለራሳቸው የተጋነነ ወይም የተሳሳት ምስል ያላቸው ሀገራት ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት እጅግ በጣም ጠንካራ እና የማይደፈሩ፣ በማንኛውም መንገድ የፈለጉትን እንደሚያደርጉ፣ ራሳቸውን ልዕለ-ኃያል አድርገው የሚያስቡ ናቸው፡፡ ይህ በመሆኑም ብዙ ጊዜ ትምክህተኝነት እና ማንአለብኝ ባይነት ያጠቃቸዋል፡፡ ያም ትምክህት ከፍ ሲል ሌላውን የመናቅ እና የማናናቅ ነገር ይታይባቸዋል፡፡ ይህም ብዙ ጊዜ የተሳሳተ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ እንዲቀርጹ ምክንያት ይሆናል፡፡ የናዚ ጀርመን፣ የሰሜን ኮሪያ፣ የኤርትራ፣ የግብጽ፣ የኢራን፣ የዚድ ባሬ ሶማሊያ ወዘተ የዚህ ሰለባዎች ናቸው፡፡ ግብጽም የዚህ ቡድን አባል መሆኗን በተደጋጋሚ አሳይታለች፡፡ አሁን ያው ግርግርም የዚሁ አካል ነው፡፡ ለራስ ከተሰጠ የግነት ምስል የመነጨ የማያዋጣ አካሄድ፡፡

በአንጻሩ ኢትዮጵያ የምትከተለው ስልት የትብብር ዓላማ መሰረቱ ሲሆን ይህም ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት በፍትሐዊነት ከውሃው ፍሬ እንዲጠቀሙ ከመልካም ጉርብትና የመነጨ እና ኃላፊነት የተሞላበት ስራ ነው፡፡ የትብብር ዓለማ ይዛ በመነሳቷም የዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድን እንዲመሰረት በማነሳሳት እንዲሁም ደግሞ ግብጽ እና ሱዳን በግድብ ግንባታው ድርሻ እንዲኖራቸው በመጋበዝ ኃላፊነቷን ተወጥታለች፡፡ የጦርነት ቃላቶች እየተወረወሩም ኢትዮጵያ በጋራ መግባባት ላይ የተመሰረተ መርህ እንዳላት አሳይታለች፡፡ ይህ ማለት ግን ነገሩን በአዋቂነት እና በጥበብ መያዟ እንጅ ሌላ ምንም ምክንያት የለውም፡፡ ይህንም የግብጽ ፖለቲከኞች ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ ነገር ግን የሙስሊም ወንድማማቾች ፖለቲከኞችም ሆነ የሰላፊስቶቹ ጩኸት ከግብጽ የረጅም ጊዜ ጥቅም አንጻር አዋጭ አይደለም፡፡ ይህ የግብግብ እና የፉክክር አካሔድ ግብጽን በተሳለ ምላጭ ላይ የመራመድ ያክል ያደማታል፡፡ ይህ የጦርነት ታምቡር የሚደለቅባቸው አካላትም-ኢትዮጵያ የሚባለውን እየሰሙ ነውና፡፡

ጥቆማ ለኢትዮጵያ እንደ ማጠቃለያ

ኢትዮጵያ የያዘችው ትብብር መር ዓላማ ዓለምአቀፍ ህግጋትን የጠበቀ እና ከጸብአጫሪነት በራቀ መልኩ እየወሰደችው ያለው እርምጃ እና መልስ የሚያስመሰግን እና የሚያኮራ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ሁሌም እንደምለው መጻኤ ሁኔታዎችን ስናሰላስል እጅግ የከፋ ነገርን አብሮ ማሰቡ የአዋቂ ነው፡፡ በዚህም እንተማመናለን፡፡ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጋራ ግንዛቤ እንዲኖረው ህዝባዊ የምክክር መድረክ እንዲደረግ መልዕክታችንን እናስተላልፋን፡፡ ከዚሁ ጋር በማያያዝ ወደ ፊት ክግብጽ ጋር ሊኖር በሚችል ድርድር ወይም ውይይት የኢትዮጵያ አቋም መሆን ያለበት የማይናወጥ እና የማይሸራረፍ ነው፡፡ ስለሆነም ከኢትዮጵያ አንጻር

የግብጽ ኮታ/ Egypt`s share ወይም አሁን ያለ የመጠቀም መብት/ Current Uses and Rights የሚሉ ነገሮች ቦታ የላቸውም፡፡ በማናቸውም መልኩ ግብጽ እነዚህን ቃላት እና ሐረጎች ለመሰንቅር የምታደርገው ጥረት በጥንቃቄ መመርመር ይኖርበታል፡፡ ስለሆነም በኢትዮጵያ የሚሰራው የታላቁ ህዳሴ ግድብ በግርጌ ሀገራት ላይ የጎላ ጉዳት እንደማይኖረው በዓለመአቀፍ ባለሙያዎች ቡድኑ የተረጋገጠ ስለሆነ ግብጽ ለምታነሳው ጥያቄ መልስ መሰረቱ ይህ ነው፡፡ ግድቡ በግርጌ ሀገራት ውሃ ፍሰት ላይ የሚያደርሰው የጎላ ጉዳት የለም የሚል፡፡ The Dam will not have significant harm to downstream water flow.

የሆነ ሆኖ በአንድም በሌላ መልኩ ሰዎች ናቸውና የግብጽ ፖለቲከኞች መሳሳት ካለ ድንገት ኢትዮጵያ አጥሯን የማጠባበቅ ስራ መስራት ይኖርባታል፡፡ ይህም እየሆነ እንደሆነ እናምናለን፡፡

በተጨማሪም አሁን ያለው የግብጽ መንግስት አካሄድ እና ንግግር የዓለምአቀፍ ህግጋትን የሚጻርር ስለሆነ ጉዳዩን ለሚመለከተው ዓለመአቀፍ አካል ማሳወቅ ተገቢ ነው፡፡ ይህንም የተባበሩት መንግስታት ጸጽታው ምክር ቤት በንቃት እንዲከታተል ማድረግ ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡

በ21ኛው ክፍለዘመን በውሃ ጦርነት እገባለሁ ብሎ መፎከር አንዳድ ጦርነት ሰባኪ ጋዜጠኞችን ከማስደሰት እና እንዲሁም ውሃ የጦርነት መነሻ ይሆናል እያሉ የሰበኩ አንዳንድ ፊደላውያንን ከማርካት የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ሰላም እና ትብብርን መሰረት ያደረገ አካሄድ መፍትሐየው ለጋራ ጥቅም ይውላል፡፡ ሀገራትም በጋራ ይበለጽጋሉ፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s