ይድረስ ለአቶ አብርሐ ደስታ የተሸወደው ማን ነው?

ዘሪሁን አበበ ይግዛው

ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ የተነሳሁት ውድ አቶ አብርሐ ደስታ “! ….. የኢትዮዽያ አቋምና የዓባይ ፖለቲካ ……!” በሚል ርዕስ በፌስቡክ ገጻቸው የጻፉት ጽሁፍ  ነው፡፡ አንደ አጋጣሚ ሆኖ በቲዊተር ስላየሁት አነበብኩት እና ትንሽ ግራ መጋባትም መገረምም አጫረብኝ፡፡ ይህ የሆነው ጸሐፊው ዋናውን ነገር ስተው ወደ መሸዋወድ ፖለቲካ ገቡና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ደ/ር ቴድሮስ አድሐኖም እንደተሸወዴ ያው ኢትዮጵያም እንደተሸወደች እንዲሁም ባለሙያወቻችን እዚህ ግባ የማይባሉ እነደሆኑ አተቱልን፡፡ የአባይን ጉዳይ ከልጅነት ጀምሮ የምከታተለው ነገር በመሆኑ አቶ አብርሐ የጻፉት ጽሁፍ ምን ውስጠ አዋቂ ቢሆኑ ነው ብየ ግራ ተጋባሁኝ፡፡ የማላውቀውን ነገር በመከተባቸው፡፡ ከዚህም ባሻገር አጻጻፈቸው ህጸጸን/fallacy መሰረት ያደረገ መሆኑን ሳስተውል ግን አይ እስኪ ውይይቱ ሳይሻል አይቀርም በሚል ብዕሬን አነሳሁ፡፡ እርሳቸው ዋናዋና በሚል መልኩ ያነሷቸውን ነጥቦች በመንተራስ እነሆ ሀሳቤን/my idea እላለሁኝ-አቶ አብርሐ፡፡

ሀ. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹን ድርድር በተመለከተ

የሰሞኑን የኢትዮጵያ እና የግብጽ በአባይ ጉዳይ ምክንያት የታየ ሞቅታ አንባቢ አንደሚረዳው ስለሆነ ወደ ዝርዝሩ አልገባም፡፡ ያም ሆነ ይህ በውስጣዊ ፖለቲካ ችግር የምትታመሰው ግብጽ ፖለቲከኞቿ የተነደገደጉበት ፉከራ እና የጦርነት ቀረርቶ ጋብ ያለው ኢትዮጵያ ድንፋታውን ከቁብ ሳትቆጥር ችላ በማለቷ በመሆኑ ይህ የሚያስመግን በመሆኑ አቶ አብርሐ እንዳሉት የኢትዮጵያ ትዕግስት የሚወደድ ነው፡፡ እንግዲህ ይህን ካልን ዘንዳ የግብጹ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚኒስቴር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው እና ድርድሩ በሰላም ተከውኖ ሀገራቱ ቀጣይ ድርድር ለማካሄድ ተስማምተው በሰላም መለያየታቸው ትክክለኛው እና ብቸኛው የአባይን ውሃ በፍትሐዊነት ለመጠቀም የሚስችል መንገድ በመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ሊወደስ እና ሊመሰገን የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ አቶ አብርሐን ያልተዋጠላቸው ጉዳይ እንዴት  ‘ዉጤታማ ውይይት’ ተደረገ የሚል አንደምታ አለው፡፡ ይህንም በጥያቄ ሲያስረግጡ  “እንዴት ዉጤታማ ውይይት ሊያደርጉ ይችላሉ? እንዴት በዓባይ ጉዳይ በአጪር ግዜ ሊስማሙ ይችላሉ?” ይሉናል፡፡ መልሱን ግን ራሳቸው ከስር መልሰውት አንደገና ወደ አጓጉል ጥርጣሬ ዘው ብለው ይሄዳሉ፡፡

የኢትዮጵያ እና የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሮች የተስማሙት በዋናነት “በቅርቡ ዓለምአቀፉ የባለሙያዎች ቡድን ባቀረባቸው የወደፊት ሀሳቦች ላይ የሶስትዮሽ ምክክር ለመቀጠል ነው፡፡” ይህ ማለት በዋናነት የባለሙያዎች ቡድኑ ቢሆኑ ብሎ አስተያየት የሰጠባቸውን ሀሳቦች ለመተግበር ነው እንቅስቃሴው፡፡ እነዚህ ሀሳቦች ምንድን ናቸው ብለን ስንጠይቅ አንደኛ ያልታዩ ጉዳቶች ካሉ እንዲመረመሩ ተጨማሪ ጥናት ማድረግ ሲሆን ይህም በዋናነት የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥናቶችን ማድረግ፣ ሁለተኛ ግድቡ ይበልጥ ለሶስቱ ሀገራት አሁን ካለው ተጨማሪ ጥቅም እንዲሰጥ ማድረግ እና ትብብርን ማጠናከር የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ምክክሩ እና ድርድሩ መቀጠል ስላለበት ድርድሩን እና ውይይቱን የባለሙያዎቹ ቡድን ባስቀመጠው መልኩ ነው አሁን የውጭ ጉዳይ ሚኒትሮቹ የተስማሙት፡፡ ይህ እንግዲህ እሰየው… ይበል በርቱ የሚያስብል ነገር ነው፡፡ አቶ አብርሐ ይህን ነገር ማስተዋል ትተው የገቡት የራሳቸውን መላምት አምጥቶ በመወተፍ ሌላ ጥርጣሬ ውስጥ እራሳቸውንም አንባቢውንም መዘወር ነው፡፡ የሀገራቱን አቋም በተመለከተ ኢትዮጵያ አቋሟን ግልጽ አድርጋለች፡፡ ግድቡ ለሴኮንድም ቢሆን ግንባታው አይቋረጥም፣ የግድቡ ውሃ የመያዝ አቅም ከ72 ቢሊዮን ኩቢክ ሜትር ዝቅ አይልም የሚሉት በዋናነት ግድቡን በተመለከተ፡፡ እንዲሁም ደግሞ አጠቃላይ የአባይ ውሃ አጠቃቀምን በተመለከተ ኢትዮጵያ ከአጼ ኃይለስላሴ ዘምነ-መንግስት ጀምሮ እንዳለቸው በቅኝ ግዛትም ሆነ በሁለትዮሽ የተፈረሙትን የ1929ም ሆነ 1959 ስምምነትን አትቀበልም፡፡ ይህም የማይናወጽ አቋም ነው፡፡ ይህንም የናይል ተፋሰስ ስምምነትን/የኢንቴቤውን ስምምነት በመፈርምም በማጽደቅም አረጋግጣለች፡፡ ታዲያ አቶ አብርሐ እነዚህ ጉዳዮች ሳይዳስሱ ሳይወያዩባቸው ሚኒስትሮቹ እርስዎ የት አምጥተው እዚህ ውስጽ ዶሏቸው?

የአቶ አብርሐ የገረመኝ አንድ ህልዮት ይህ ነው፡፡ “ቀደም ሲል ‘በዓባይ ጉዳይ በቀላሉ መስማማት የሚቻለው ቢያንስ አንደኛው ወገን ብሄራዊ ጥቅሙ አሳልፎ ሲሰጥ ብቻ ነው’ የሚል መልእክት ያለው ሓሳብ አስፍሬ ነበር።” ይላሉ፡፡ ይህ ለእኔ እንግዲህ እሚዋጥ አይደለም፡፡ አሁን ያለው የተፋሰሱ ሁኔታም ይህን የሚፈቅድ አይደለም፡፡ ሀገራቱ ብሐራዊ ጥቅማቸውን አሳልፈው ስለሚሰጡ አይደለም የአባይ ጉዳይ የሚፈታው፡፡ ሁሉም ሀገራት ብሔራዊ ጥቅማቸውን ባስጠበቀ መልኩ በሚያደርጉት ውይይት እንጅ፡፡ አቶ አብርሐ እያሉን ያሉት የዜሮ ድምር ጨዋታን  ነው፡፡ እሱ ጨዋታ እኮ ቆየ ከተቀየረ አባይ ተፋሰስ ላይ፡፡ ሁሉም ሀገር በዚህ አቋም አንዲትም እርምጃ መራመድ አይችልም፡፡ ምክንያቱም የተናጠል ስራን ያገናልና በዋናነት ተጠቂዎቹ እነማን እንደሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ለዚህም ነው እኮ የግብጽ ውሃ ሀብት ልማት ሚኒስቴር የነበሩት እና በላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ዘንድ ከበሬታ ያላቸው ደ/ር መሐመድ አቡ ዛይድ በአንድ ወቅት ከታይም መጽሄት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በአባይ ውሃ ላይ የላይኞቹን ሀገራት አትጠቀሙ ብለን መከልከል አንችልም፡፡ ሆኖም ግን እንዴት የሀገሮቻችንን ጥቅም አስማምተን መሄድ እንዳለብን መተባበር ነው፡፡ ያሉት፡፡ ሌላው አቶ አብርሐ በድርድር ሂደት ውስጥ ሰላምን ለማምጣት እና በጋራ ለመጠቀም ሌላ አማራጭ መፍትሔ እንዳለ ያጡታል ብዮ አላምንም፡፡ አላስብምም፡፡ እስኪ ትንሽ የጨዋታ ህልዮትን/ Game Theory የምትባለዋን ነገር በደንብ ይመልከቷት፡፡ ምን ያዋጣል… ይህን ብንመርጥ ምን ይቀርብናል.. ምንስ እናገኛለን… ሌሎቹ ሀገራትስ ምን ይመልሳሉ… ምን ያደርጋሉ… ወዘተ እያሉ የጨዋታ ህልዮትን ይዳስሳሉ፡፡ እናም የተሸለ የሚሉትን ካለው ነባራዊሁኔታ እና የሀገራት ስልት ጋር በማስተያየት የራሳቸውን ስልት ይነድፋሉ፡፡ ከዚህ አንጻር የዜሮ ድምር እሳቤው አካሄድ የትም አያደርሰም፡፡ ለዛም ነው ትብብር እ ድረድር ብለው የተፋሰሱ ሀገራት ላለፉት 14 ዓመታት አብረው የዘለቁት፡፡ ይህ ማት ግን ስምምነት አለ ማለት አይደለም በሁሉም መስክ፡፡ ያም ሆነ ይህ አቶ አብርሐ ደስታ በራስዎ እሳቤ እና ፍላጎት ወይም ምልከታ ድርድሩን ስለሰፈሩት አንደትርጓሜዎ ከሆነ “ስምምነቱ ተግባራዊ ከሆነ የኢትዮዽያ መንግስት ተሸንፏል ማለት ነው። ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በትክክል ተሸውዷል።” የተሸወደው ግን ማን ነው? እርስዎ አይደሉምን?! ለምን?

አንደኛ አቶ አብርሐ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ መካከል የነበረውን ውይይት ፍሬ ሀሳብ አልያዙትም፡፡ አልተረዱትም፡፡ የባለሙያዎች ቡድኑ የጠቆማቸውን ሀሳቦች ለመተግበር ድርድሩን ለመቀጠል ነው ሚኒስትሮቹ የተስማሙት እርስዎ ግን ሌላ ቦታ ገብተዋል፡፡ አንድ ነገር ላስታውስዎ፡፡ ይህ ቡድን እንዲቋቋም ሀሳብ ያቀረበችው ኢትዮጵያ ናት በጥሩ የወንድማማችነት እና ጎረቤትነት መንፈስ፡፡ ይህም የሚያሳየው ሀገሪቱ ያላትን በራስ መተማመን የሚያሳይ ነው ልብ ብለው ቢያስተውሉት፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የባለሙያዎች ቡድኑ ለሶስቱ ሀገራት መንግስታት (ግብጽ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ) ሪፖርቱን ባቀረበበት ዕለት የኢትዮጵያ ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር እንዲህ ብሎ ነበር በመግለጫው፡-

አለም አቀፉ የባለሞያዎች ቡድን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለሶስቱ የተፋሱ አገሮች ግብጽ፣ሱዳንና ኢትዮጵያ የሚሰጠውን ጥቅም፥ እንዲሁም ግድቡ በሁለቱ የታችኛው የተፋሰሱ አገሮች ላይ የሚያደሰው ጉዳት ካለ የፕሮጀክቱን የጥናት ሰነድ በመመልከት፥ በጥናት ሂደት ውስጥ ያልታዩ ወይንም በደንብ ያልተዳሰሱ ጉዳዮች ካሉ ለይቶ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ መንግስት አስፈላጊውን የማስተካከከያ እርምጃ እንዲወስድ ሀሳብ የማቅረብ ሃላፊነት የተጣለበት አካል ነው፡፡

ይህ ማለት አቶ አብርሐ ግድቡን አቁሙ ይላሉ ማት አይደለም፡፡ ሳይንስን መሰረት አድርጎ የሚሰራ ስለሆነ ጉዳጥ ካለ አንዲህ አድርጉ ከተባለ እስከታመነበት ድረስ ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም ከመጀመሪያው ጀምሮ ኢትዮጵያ ግልጽ እንዳደረገችው ግድቡ የሚገነባው ሌሎቹን ሀገራት በመጉዳት ኢትዮጵያን ብቻ ለመጥቀም ሳይሆን ኢትዮጵያ የሌሎቹ ሀገራት የውሃ ፍላጎት ላይ የጎላ ጉዳት ሳታደርስ ውሃውን መጠቀም እንዲሁም የሁለቱን የግርጌ ሀገራት ተጠቃሚነትም ማረጋገጥ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ድርድር የዚህ ሂደት አካል እንጅ ሌላ ጉዳይ የለውም፡፡ ሌላ በዚሁ መግለጫ ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የባላሙያዎች ቡድኑን አጠቃለይ ሪፖርት በሚገባ በመመርመር ለወደፊቱ ትብብሩ የሚቀጥልበትን መንገድ እናሳውቃለን ብሎ ነበር፡፡ እናም የተሸወዱት እርስዎ  ነዎት፡፡ ልብ ብለው ይመርምሩት ጉዳዩን፡፡

ሁለተኛ አቶ አብርሐም የዘነጉት ነገር ደ/ር ቴድሮስ እንዲህ አይነት ድርድር ላይ ብቻቸውን የተዋያዩ የመሰላቸው መሰለኝ፡፡ ወይም ደግሞ በዙሪያቸው ድጋፍ ሰጪ ዋና የመስኩ ባለሙያዎች የሌሉ ያክል  ነው የቆጠሩት፡፡ ወይም ደግሞ ቢኖሩም ዋጋ የላቸውም በግብጾች ተብልተዋል ዕውቀቱ ስሌላቸው ዓይነት እሳቤ እንዳለ ከስር ገልጸውልናል፡፡፡ ይህም ስህተት ነው፡፡ ከዚህ ላይ ማለት የምፈለገው ቢኖር አቶ አብርሐ ሃሳብ ገብቶዎት ከሆነ ሊሰመርባቸው እና ሊታሰብባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ብለው ሃሳብዎን ባቀረቡ ነበር፡፡ ነገር ግን ነገርን አጩሆ ተሸወደ ተሸወድን ብሎ ማለት በራሱ ስህተት ይመስለኛል፡፡ እጅግም ነው፡፡ የሚበጅ ሃሳብን ማካፈል አንድ ነገር ነው፡፡ ዘሎ ነገሩን ልብ ብለው ሳይረዱ ወቀሳ እና ከሰሳ ላይ መግባት እርስዎን ትዝብት ውስጥ ይጥልወታል፡፡ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ጉዳዮ ብለው የያዙት ሰዎች እንዳሉም አይዘንጉ፡፡ እርስዎ እንዳሉት ቢሆን ኖሮ አገር ይነቃነቅ ነበር፡፡ እኔን ጨምሮ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ዘወር ብለው የጻፉትን ነገር ያስቡት ደጋግመው የተሸወዱት እርሰዎ ነዎትና፡፡

ሶስተኛ እንደ አቶ አብርሐ ሀተታ የሸወደችን ግብጽ ናት፡፡ ምነው እና ግብጽን አልተሸደችም? ልብ ይበሉ አቶ አብርሐ የእርሰዎን ህልዮት ይዤ ነው የምጠይቅዎ፡፡ አንዲህ ማለትዎን አይዘንጉ ‘በዓባይ ጉዳይ በቀላሉ መስማማት የሚቻለው ቢያንስ አንደኛው ወገን ብሄራዊ ጥቅሙ አሳልፎ ሲሰጥ ብቻ ነው’፡፡ በርሰዎ እይታ ኢትዮጵያ ተሸናፊ ወይም ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ የምትሰጥ ግብጽ ደግሞ ተሟሟች ናት፡፡ ይህ ለእኔ የመንፈሰዊ ልዕልና ጉዳይ ነው፡፡ ራን ዝቅ አድርጎ የማየት እና ሀገርን የማሳነስ፡፡ ሌላ ጉዳይ ላይ ስለደገሙት እመለስበታለሁኝ ከስር፡፡ አንድ ነገር ግን ላስምር እኔ እስካሁን ያየሁት እና እየሆነም ያለው ኢትዮጵያ እንዳለቸው  ነው፡፡ የባለሙያዎች ትብብሩ ይቋቋም አለች-ተቋቋመ፤ ሀሳቡን በማቅረብ ሀገራቱ ይወያዩ፤ይመካከሩ አለ.. ኢትዮጵያ ይን አለች፡፡ ሆኖም እነ ሞርሲ የጦርነት ታምቡር ደለቁ… መለኸት አስነፉ… ወዘተ ወዘተ.. በዚህም ምክንያት ድርድሩ እና ምክክሩ መስተጓጎል ገጠመው፡፡ ከዛ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መሀመድ ከማል አሚር  ኢትዮጵያ መጡ ከአቻቸው ከደ/ር ቴድሮስ ጋር ተነጋገሩ ምክክሩ ይቀጥል ተባብለው ተስማሙ፡፡ እውነታው ይህ ነው፡፡ የሸወደም የተሸወደም የለም በሀገራቱ መካከል፡፡ ያም ሆነ ይህ አሁንም ሃሳብዎን ያጢኑት ዘንድ አደራ እልወታለሁ፡፡ የተሸወዱት እርስ ነዎትና!!

ለ. የኢትዮጵያ ባለሙያዎችን በተመለከተ

እንደ አቶ አብርሐ ገለጻ ኢትዮጵያ በፖለቲካም ሆነ የቴክኒክ ጉዳዮችን ጠንቅቀው የሚያውቁ ባለሙያዎች እንደሌሏት ነገረውና እንዲህ ሲሉ፡- “ኢትዮዽያ ብቁ የቴክኒክና የፖለቲካ ተደራዳሪዎች የሏትም፡፡” ልጠይቅዎ እስኪ ምን ዓይነት ጥናት አድርገው የደረሱበት ድምዳሜ ነው ይሄ? የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ላይ የነበረው ሁኔታ ለአባይ ጉዳይ ማንጸሪያ ሆኖ መቅረብ ነበረበት ወይ? ምን ያክልስ የኢትዮጵያ ውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትርን ያውቁታል? ምንያክልስ በናይል ተፋሰስ የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ ላይ ተደራደሪዎቻችን ምን እንደሰሩ እነማን አንደነበሩ ያውቃሉ ወይ? ለዚህ ድምዳሜዎ ማረጋገጫዎ ምንድን ነው? እኔ ግን እልወታለሁ…

በዚህ ጉዳይ ኢትዮጵያን አያውቋትም፡፡ ከላይ አንደጠቀስኩት ይህ አንደኛ የመንፈሳዊ ልዕልና ጉዳይ ነው፡፡ ለራስ የሚሰጥ ምስል ጉዳይ፡፡ ስለራስ ያለ ግንዛቤ ጉድለት፡፡ ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት በዓባይ ተፋሰስ ላይ ጥናቴን ሳካሂድ እጅግ የሚያስደምሙ እና የሚያኮሩ ሰዎቸን አግኝቻለሁ፡፡ አንቱ ከተባሉ የሜትሮሎጅ ሳይንቲስቶች እስከ የውሃ ኢኮኖሚስቶች፣ ከውሃ ፖለቲካ ተንታኞች እስከ የዓለምአቀፍ የውሃ ህግ ባለሙያዎች፣ ሀይድሮሎጅስቶች፣ የውሃ መሐንዲሶች ወዘተ… በአንድም በሌላም መልኩ ኢትዮጵያን ወክለው የናይል የትብብር ስምምነት ማዕቀፍ ስምምነት ላይ ከተደራደሩ ኢትዮያውያን ውስጥ አራቱን በቅርብ የማውቃቸው እና የማከብራቸው ሰዎች ናቸው፡፡ እናም እነሆ እኔ ምስክር ሆንኩ፡፡ ራስን ጭቃ የሚያደርግ ሁሉ ይረገጣል ይል ነበር አንድ ወንድምሁነኝ እዘዘው የሚባል የቀለም ቀንድ የሆነ አብሮ አደጌ፡፡ እናም አቶ አብርሐም መጀመሪያ ቀርበው ይዩ፡፡ እነማን አሉ ይበሉ፡፡ ከዛ ትችቱንም ምኑንም ይቀጥሉ፡፡ ሳያውቁት ውስጡን እንዲህ የራስን ማሳነስ ያስተዛዝባል፡፡ ሊቁ አቡነ ሉቃስ በአንድ ወቅት አንዲህ ብለው ነበር ቁጥሩን በትክክል ማለቴን እንጃ ግን ሀሳቡን ብቻ ልበል፡፡  አንድ ሌባ አንዲት ሴትዮ ቤት ይገባና የተወሰነ ብር ይሰርቃል፡፡ ወደ ሃያ ብር ገደማ ነው፡፡ ሌባው ጠፋ፡፡ ጎረቤት ቢጤ ነው፡፡ ከዚያ ሴትዮዋ አገር ይያዝልኝ ብሬ ጠፋ ብለው ኡኡታወን አቀለጡት፡፡ በመቀጠል ሰዎች ተደናግጠው ስንት ብር ነው የጠፋ እማማ ምን ያክል ነው? ይረጋጉ ይሏቸዋል፡፡ ሴትዮዋም ሌባው የለም ብለው ሃምሳ ብር ብለው እርፍ፡፡ ይህኔ ሌባው ኸረ ተው ሌባም ይታዘባል፡፡ አሏቸው አሉ፡፡ እናም ውድ አቶ አብርሐም በዚህ አገላለጽዎት ግብጾቹም ይታዘባሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ አንድ ነገርን ማለት ወደድሁኝ፡፡ ግብጻውያን ብዙ ውሃ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎች አሏቸው፡፡ ይህ እርግጥ ነው፡፡ በዚያው ልክም እጅጉን ይጋነናል፡፡ እነሱም ለራሳቸው ያጋነሉ እኛም ስለ እነሱ እናጋናለን፡፡ ይህም በውሃ ባለሙያዎች ብቁ ነን ባይነታቸው ወደ ትምክህተኝነት ስለወሰዳቸው ግብጾቹ የግድቡን ጥንካሬ እኛ እንመርምረው አሉ፡፡ ሊበሏት ያሰቧትን እንዲሉ፡፡ በነገራችን ላይ የግብጹ የታላቁ አስዋን ግድብ ሲሰራ የቴክኒክ ባለሙያዎቹ በዋናነት ራሻውያን ነበሩ፡፡ አቶ አብርሐምን አንድ ተስፋ ልነግርዎት ወደድሁኝ በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ውስጥ እና ከኢትዮጵያ ውጭ ውሃ ላይ የሚሰሩ በተለያየ የጥናት መስክ እያስመሰከሩ/specialize እያደረጉ/ ያሉ እጅግ ብዙ ኢትዮያውያን አሉ-በሁሉም ከውሃ ጋር በተያያዙ መስኮች፡፡ ስለሆነም አይሳሳቱ ለማለት ያክል ነው፡፡

ለማጠቃለል ያክል ጉዳዩ ታላቅ አጀንድ እና ሀገራዊ ጉዳይ ስለሆነ ከጥርጣሬ እና ከራሳችን መላምት ወጥተን ሀገርን እንደ ሀገር መደገፍ ላይ ብናተኮር መልካም ነው፡፡ አበቃሁ!!!

Advertisements

6 thoughts on “ይድረስ ለአቶ አብርሐ ደስታ የተሸወደው ማን ነው?

  1. ዘሪሁን እጅግ በጣም አመሰግንሃለሁ:: በደንብ አድርገህ አስተማርከዉ:: ለነገሩ እሱ ይህ ጠፍቶት አይመስለኝም:: ሆነ ብሎ ነዉ:: በተለይ ደግሞ እሱን የሚከተሉ እዉቀቱ ሳይኖራቸዉ እንዲሁ ድግፍ እንደሚሰጡት ጠንቅቆ ስለሚያዉቅ ነዉ እንድዚህ አይነት ነገር የሚጽፍዉ:: ትላንት ማታ ከኔ ጋ ብዙ ምልልስ ሰናደርግ ከደጋፍዎቹ ብዙ ስድቦችን አስተናግጃለሁ:: እሱም ፈጽሞ ስህተቱን ሊያምን አልፈለገም ነገር ግን ብዙ መረጃዉ የለላቸዉን ሰዎች እያሳሳተ ነዉ ::

    እግዜር ዕድሜ ይስጥህ ከማለት ዉጭ ላንተ ምንም ነገር አድናቆት ባቀርብልህ አይበቃኝም:: በጣም ጥሩ አርግህ ነዉ የጻፍከዉ:: በርታ!

    1. OH Girmaye.. thank you brother.. your kind words are always inside me.. and keeps me walking… thank you…

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s