የሞርሲ መንግስት መወገድ፡ ዕድል እና ተግዳህሮቶች (ክፍል ሁለት)

ዘሪሁን አበበ ይግዛው

በመጀመሪያው ክፍል የግብጽ ህዝባዊ መፈንቅለ-መንግስት እና የናይል ውሃ ጉዳይ፡ ከሞርሲ በኋላስ? በሚል ርዕስ በዋናነት የሞርሲ መንግስት የአባይ ፖሊስ በመሰረቱ የቀደመውን እና ከሙባርክም ሆነ ከሙባርክ በፊት የነበረን የግብጽ ግትር የናይል ፖሊሲ እንዲሁም ዛቻ እያይዞ የቀጠለ መሆኑን ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ሁለት አበይት ጉዳዮች ላይ ወፍ በረር ቅኝት እናደርጋለን፡፡ አንደኛው የሞርሲ መንግስት መውደቅ ያለው በጎ አስተዋጽኦ ከናይል ተፋስ አንጻር ሲሆን ሁለተኛው የሞርሲን መንግስት ተከትሎ ስለመጣው የሽግግር መንግስት ሁኔታ ዕድሎችን እና ተግዳህሮቶችን እንቃኛለን፡፡ ሆኖም በመሐል በሞርሲ አስተዳደር ዘመን ስለነበረው የድርድር ጅማሮ ይጠቀሳል፡፡

የፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሞርሲ መወገድ ለግብጽ በዋናነት በመቀጠል ለምስራቅ አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ በጎነት በውስጡ ይዟል፡፡ ማን እንደሚመራቸው የሚውስኑት ግብጻውያ ራሳቸው ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በበርም ይን በጓዳ ይግባ ሀገሪቱን የሚመራ/በአገዛዝ ወንበር ላይ ያለ አካል በአንድም በሌላም መልኩ የሚከተለው የውጭ ግንኙነት እና ዓለምአቀፍ ፖለቲካ አመለካከት የሚመለከታቸው ሀገራት ስላሉ ነገሩን ከዚሁ አንጻር አስተያየት መስጠት ተገቢ ይመስለናል፡፡ ስለሆነም ለ80 ዓመታት አንድ እባብ እናት እናቱን እየተባለ ያልጠፋው የሙስሊም ወንድማማቾች በግብጽ ወደስልጣን ብቅ ማለት በአንድም በሌላም መልኩ የግብጽ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ ለአንድ ዓመትም ቢሆን አሻራውን ጥሎ አልፏል፡፡ ከዚህ አንጻር የአባይ/የናይል ውሃ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ የሞርሲ መንግስት በመጀመሪያው ክፍል አንደተዳሰሰው ያለአግባብ እና ትምክህተኝነት እና የማይበጅ ማንአለብኝነትን ገሀድ ባወጣ መልኩ የተሰሙት ተደጋጋሚ ዲስኩሮች በአንድም በሌላም መልኩ የግብጽን ከናይል ተፋሰስ ሀገራት ጋር የሚኖር ግንኙነት እጅጉን ሸካራ ያደርግ ነበር፡፡ በተለይ ፕሬዝዳንቱ እና መንግስታቸው የአገዛዙን መንበር እንደያዙ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ትንሽ ጉዳቱ ከፍ ይል ነበር፡፡ ይህም በዋናነት ሁለት መሰረታዊ ነገሮች ላይ የቆመ ነበር፡፡ አንደኛው የህግ አውጭወን አካል ከተቆጣጠሩት ፓርቲዎች አንጻር የሚመነጭ ሲሆን ሁለተኛው እና ተያያዡ ጉዳይ እነዚህ ፓርቲዎች ያላቸው ንጽሮተ-ዓለም ነው፡፡ ይህን የምናነሳባት ዋናው ጉዳይ ህግ-አውጭው አካል የስራ አስፋጻሚውን ተጽእኖ ባንድም በሌላ መልኩም ስለሚያሳድር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ስናይ የግብጽ የላይኛው ምክር ቤት በዋናነት ካሉት 180 መቀመጫዎች ውስጥ ብዙውን ኢስላማዊ አክራሪነትን በሚያራግቡት የሙስሊም ወንድማማቾቹ የሰላም እና ፍትሕ ፓርቲ (106) እንዲሁም የሰላፊያው ቡድን ፓርቲ አል-ኑር (46) የተያዘ ነበር፡፡ የአክራሪነት አጀንዳ በገሀድ የሚያጸባርቁት እነዚህ አካላት ያላቸው ንጽሮተ-ዓለምም የተንሸዋረረ እና በዚሁ መስመራቸው የተቃኘ  ነው፡፡ ለምሳሌ ያክል ከቤተ-መንግስት በቀጥታ በስህተትም ሆነ ታስቦበት በተላለፈው ውይይት ላይ እነዚህን ነገሮች እናስተውላለን፡፡  ከናይል ወንዝ አንጻር እንግዲህ ሰላማዊ መንገድን አንከተላለን ስላሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሂሻም ቀንዲል በዚህ ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ ሲሰጡ መወረፋቸውን ማስታውስ ግድ ይሏል፡፡

ከዚሁ ከንጽሮተ-ዓለም ጋር በተያያዘ የምናገኘው ሌላኛው ጉዳይ የእነዚህ ፓርቲዎች ያላቸው ወይም የለመደባቸው እስራኤልን እና የናይልን ውሃ የማተሳሰር ነገር ነው፡፡ ይህንም በቀጥታ በተላለፈው ውይይት ላይ ሲጠቀስ እንሰማለን በአል-ኑር ፓርቲው ሊቀመንበር ዛካሪያ ዩኑስ አበድል-ሃሊም ማክዮን፣ በአል-አዘሃሩ ሼክ ሀሰን አል-ሻኤፍ እንዲሁም የኢስላሚክ ሌበር ፓርቲው ማግዲ አህመድ ሁሴን:: በሌላም መልኩ የእነዚህ ኃይሎች የምስራቅ አፍሪካ የሚያዩበት መነጽር እንዲሁ የተንሸዋረረ ለመሆኑ ማሳያ በተለያያ ጊዜ የሙስሊም ወንድማማቾች በእንግሊዘኛ ድረ-ገጹ ያወጣቸውን ጽሁፎች መመልከቱ ጠቋሚ ነው፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾች በሱዳንም እንዳለ ሁሉ በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮችም እንዲስፋፋ ፍላጎቱ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ በ2006 እኤአ ወደ ሶማሊያ መግባት ተከትሎም የሙስሊም ወንድማቾች ለሶማሊያው ኢስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት አጋዥ የሆነ መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ በጥቅሉ እጅጉን ባህልን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ ሌላ ግጭት ወይም የጥቅም ፉክክር ሊነሳ እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡ ከዚሁ ጋር የሚያያዘው በኢትዮጵያ እግሩን እና እጁን ብቅ ብቅ እያደረገ ያለው የሳላፊያ እንቅስቃሴም ለዚሁ ዓላማ መጠቀሚያ ፈረስነት አያመልጥም ነበር፡፡ በሀሰን አልቱራቢ በሱዳን እንዲሁም በደ/ር አሊ ባሻ በሶማሊያ የሚመሩትን ሙስሊም ወንድማማቾች  ስናስብ የሚሰጠን የራሱ የሆነ ምስል አለ፡፡ በተጨማሪም ከአሁን በፊት እንደጠቀስሁትም የቱርክ የሶማሊያ እንቅስቃሴም ከዚሁ አንጻር የሚታይ ነው፡፡ ያለነገርም እኮ አይደለም የቱርኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጠይብ ኤርዶጋን ሞሐመድ ሞርሲ ፕሬዝዳቴ ነው ያሉት፡፡  ይህ ሁሉ ነገር ተደምሮ ለናይል ውሃ ድርድር እንቅፋት መሆኑ አይቀሬ ነበር፡፡ ይህ ማለት ግን የአክራሪነት አጀንዳ ያላቸው የእነ ሞርሲ መንግስትነት አክትሟልና ከተግዳሮት ነጻ የሆነ መወያያ መድረክ ተፈጥሯል ማለትም አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ነገር ቢኖር የሞርሲ መንግስት የቅርብ እረዳት እና አጎብዳጅ የነበረው አጅግ አክራሪው የሰለፊያው አል-ኑር ፓርቲ የፖለቲካ እክሮባቱን በማጠንከር ከሽግግር መንግሰቱን ተቀብሏል፡፡ ዞሮ ዞሮ በሚደረግ ምርጫ እነዚህ ቡድኖች ተመልሰው ወደ ስልጣን ከመጡ የተፈራው ነገር መመለሱ አይቀርም፡፡ ስለዚህም ይህን እያሰቡ መራመድ አስተዋይነት ነው፡፡  ምንግዜም ቢሆን በወሰን ተሸጋሪ ወንዞች ላይ በሀገራት መካከል የሚደረጉ ድርድሮች እና ውይይቶች በውሃ ፖለቲካ ታሪክ፣ የአቅም ሚዛን፣ ኢኮኖሚ እና ወታደራ ኃይል፣ መልከአ-ምድር፣ ሐይማኖት እና ባህል፣ ንግድ፣ የመንግስታት/አገዛዝ ዓይቶች እና ባህሪ ወዘተ ጥላ ለበጎም ለክፉም የሚያርፍባቸው ናቸው፡፡ ስለሆነም የሙስሊም ወንድማማቾች በዚህ ሰዓት ከፖለቲካው ዋና ተዋናይነት ገለል ማለት የራሱ የሆነ በጎ ገጽታ እንዳለው እንረዳለን፡፡

በሌላ መልኩ በሙርሲ ይመራ የነበረው መንግስት መወገድ በራሱ ተግዳህሮቶችን ይዞ መምጣቱ አልቀረም፡፡ በሞርሲ መንግስት አስተዳደር ውስጥ በአባይ ውሃ ጉዳይ ላይ አራት ቁልፍ ሰዎችን እናስተውላለን፡፡ አንደኛ ፕሬዝዳንቱ፣ ሁለተኛ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሶስተኛ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዲሁም አራተኛ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ በናይል ውሃ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ እነዚህን ሰዎች እናውቃቸዋለን፡፡ በተለይ የውሃ እ መስኖ ሚኒስትሩ ሞሐመድ ባሐ ኤል-ዲን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሞሐመድ ካሜል አምር፡፡ ነገሮች ጡዘው በነበሩነት እና የቀድው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሞርሲ የውስጥ ጉዳያቸውን ወደ ውጭ ለማቀየስ በጣሩበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከኢትዮያው አቻቸው ደ/ር ቴድሮስ አዳህኖም ጋር ለድርድር የተቀመጡት ሞሐመድ ካሜል አምር የሞርሲን የመጨረሻ ንግግር ተከትሎ ስልጣናቸውን መለቀቃቸውን አሳውቀው ነበር፡፡ ሆኖም የሽግግር መንግስቱ እስኪሰየም ድረስ በመቆየት ለሽግግር መንግስቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነቢል ፋሚ አስረክበዋል፡፡ ምንግዜም ቢሆን የተረጋጋ መንግስት ከለለ እና ስራ አስፈጻሚዎቹ አካላት በተለያየ ምክንያት በተቀያየሩ ቁጥር በድርድር እና ውይይት የራሱ የሆነ ተጽእኖ አለው፡፡ ይህ የሞርሲ መንግስት ካቢኔ መፍረስ ያስከተለው አንድ ተግዳህሮት ነው፡፡ ድርድሩን የሚያካሂዱት አካላት ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን ዕለት ዕለት በጉዳዩ ዙሪያ እየተገናኙ እን እያወሩ በመጡ ቁጥር ወዳጅነትም ጓደኝነትም ወንድማማችነትም ሊመሰረት ይችላል፡፡ ይህም በጎ የሆነ የድርድር መንፈስን እና መተማመንን ሊያመጣ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

በዶ/ር ቴድሮስ እና በሞሐመድ ካሜል አምር መካከል የታየው በጎ የሆነ በህዳ ግድብ ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታት የተደረገ የድርድር ሂደት በጎ ጎኖችን ይዞ ብቅ ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እና ግብጽም ሱዳንን በመጨመር የዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድኑ ባቀረበው ሀሳብ መነሻነት ድርድሩን እና ውይይቱን ለመቀጠል ተስማምተው ነበር የተለያዩት፡፡ በመሐል ግን የግብጽ ውስጣዊ የፖለቲካ ሁኔታ ባለመፍቀዱ ነገሮች እንደታሰበው አልሄዱም፡፡ የሆነ ሆኖ በግብጽ አዲሱ የሽግግር መንግስት አዲስ ፕሬዝዳንት አድሊ መንሱር፣ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር- ሀዜም ኤል-ቤብላዊ፣ አዲስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነቢል ፋሚ እንዲሁም አዲስ የመስኖ ሚኒስትር ሞሀመድ አበድለ ሙጣሊብን እንዲሁም መከላከያ ሚኒስትሩን ጄኔራል አበድል ፋታህ አል-ሲሲን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትሞሐመድ አል-ባራዳይን ደግሞ የውጭ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ ይዟል፡፡ የእነዚህ ሰዎች ወደዚህ ቦታ መምጣት የራሱ የሆነ አንድምታ አለው፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤብላዊ የመንግስታቸው አንዱ ትልቅ ስራ ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ባለቸው የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለ አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነቢል ፋሚም በመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ኢትዮጵያን ከመምጣታቸው ስንጠራት አቤት አልለን አለች በሚል መንፈስ መክሰሳቸው ውይይቱን እና ድርድሩን በገንቢነት ከመቀጠል ይልቅ ወደ ኋላ ይጎትተዋል፡፡  የሆነ ሆኖ አዲሱ ውጭ ጉዳይ ሚኒትር አያይዘው አዲስ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ አፈሪካን እና ጎረቤት ሀገሮችን መሰረት በማድረግ እንደሚቀርጹ አስረድተዋል፡፡ ይህ ከሆስኒ ሙባርክ መንግስት ውድቀት ማግስት ጀምሮ በተደጋጋሚ የተለፈፈ ጉዳይ ቢሆንም ተግባራዊ ግን አልሆነም፡፡ ለምሳሌ ከሞርሲ መመረጥ በፊት የነበረው የኤሳም ሻራፍ የሽግግር መንግስት በመስከረም 2011 ኢትዮጵያ እና ግብጽ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ እንደሚከፍቱ ገልጸው ወደኋላ መመለስ እንደማይቻል እንዲሁም የቀደመው መንግስት የተሳሳተ ፖሊሲ ቀርጾ ይንቀሳቀስ እንደነበር አክለው ወደ ኋላ መመለስም እንደሌለ አስረድተው ነበር፡፡ ይሁን እና በአፍ የሚባለው ነገር ከሚደረገው ነገር ነገር ጋር ገጥሞ አልተስተዋለም፡፡ የሞርሲ መንግስትም እንዲሁ አስተጋቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በተግባር የሆነው ያ ቀድሞ በሙባርክ እና ሳዳት ዘመን የነበረው የከፋፍለህ ግዛ እና የቀረርቶ ፖሊሲ ነበር፡፡

በእርግጥ አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ይዘውት የመጡት ነገር ግብጽ የውሃ ዋስትና ፖሊሲዋን እንደገና መፈተሸ አለባት ማለታቸው ነው፡፡ በዚህም መሰረት የውሃ ዋስትና የሚለው ሐረግ አንድገና ትርጓሜ እንደሚያሻው ገልጸዋል፡፡ ምን ዓይነት የሚለው ግን ወደፊት የሚታይ ነው፡፡ ነገር ግን የውሃ ዋትናነት ከብሔራዊ ድህንነት ጉዳይ ጋር በማተሳሰር እና ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ፍቺ እንዲኖረው የሚደረግ ከሆነ ዞሮ ዞሮ እዚያው ነው የሚሆነው፡፡ የውሃ ዋስትና በመሰረቱ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር እንዲሁም ውሃን ፍትሐዊ እና ምክንያዊ በሆነ መልኩ ከመጠቀም መርህ ጋር ተያይዞ ሲበየን ወይም ሲተረጎም የተፋሰሱን ሀገራት ወደ ሰላም እና ትብብር ይወስዳል፡፡ ሆኖም ግን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ብያኔ ከተሰጠው ልዩነትን ማፋቱ በተግባር የታየ  ነው፡፡ ግብጽ ነቢል ፋሚ እንዳሉት የውሃ ዋስትና ጉዳይ እንደገና መመርመር ያለበት ይህም በጎ የሆነ አቀባበል የሚኖረው ነው፡፡ ሆኖኖም ግን ነቢል ፋሚ በ2011 ሚያዝያ ወር ላይ ስለ ናትስማ (የእንቴቤው ስምምነት) አስተያየት ሲሰጡ ይህ ስምምነት በመፈረሙ የናይል ተፋሰስ እንደ ቀድሞው አለመሆኑን ይናገረላ፡፡ ሆኖም ግን ነቢል ፋሚ የዚህን ስምምነት ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ ከመቀበል ይልቅ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ያላቸውን ብዙ ውሃ የሚያጠራቅሙበትን መንገድ መፈለግ አለብን ይላሉ፡፡ በዚሁ አስተያየታቸው ላይ የላይኛው ተፋሰስ የውሃ ፕሮጀክቶች ለኤሌከትሪክ ማመንጫ ይሁኑ እንጅ ዲዛይቻቸው ወደ ግብጽ ውሃ እንዳይሄድ ለማድረግ ወይም ለመቆጣጠር እንዲያች ተደርጎ ሊሰራ ይችላል ሲሉ የተሳሳተ ጥርጣሪያቸውን ይገልጻሉ፡፡ አለመተማመን እና ጥርጣሬ ካለ እንዴትስ ትብብር ሊመጣ ይችላል፡፡ የእኒህ ሰው አስተሳሰብ በመሰረቱ በካይሮ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ካሉት እንደ እን ሞሐመድ ነስር አል ዲን አላም የተለየ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ የሆነ ሆኖ የውሃ ዋስትናን እንዴት እንደሚተረጉሙ እንዲሁም ደግሞ በሀገራቱ መካከል በሚደረገው ድርድር ለውጦቹ የሚታዩ ይሆናል፡፡

ለማጠቃለል ያክል በወሰን ተሸጋሪ ወንዞች ዙሪያ በሚደረግ እሰጣ-ገባ ውስጥ አንዳንድ ጸብ-አጫሪነት የሚያጠቃቸው መሪዎች መወገዳቸው ለአጠቃላይ ተፋሰሱበጎ የሆነ አንደምታ ቢኖረውም የራ የሆኑ ተግዳሮቶችም አሉት፡፡ በዋናነትም ቶሎ ማለቅ የሚችልን የድርድር ሂደት ማራዘሙ የግድ ነውና፡፡ ውይይት እና ድርድር ሰዎችን መሰረት አድርጎ የሚካሄድ በመሆኑ በሰዎች መካካል በጎ የመግባባት እና የመወያየት መንፈሶች ሲኖሩ ድርድሩን ያግዛሉ፡፡ ምንም እንኳን በፊትም የነበሩም ሆነ ያልነበሩ ባለሙያዎች ፖለቲከኞችን ከጀርባ በመሆነ የሚያግዙ እና ዋናውን ስራ የሚሰሩ ቢሆንም በፖለቲከኞች መካከል ያለ ግንኙነት የነገሮች ሁሉ ማሳረጊያው ነው፡፡ ምንግዜም ቢሆን ሳይንስ እና ባለሙያዎች መደራደር እና መወያየት እንዳለ ቢያሳኑም፣ የተለያየ የመፍትሔ ሀሳብ ቢያቀርቡም የሀገራቱ የፖለቲካ ውሳኔ የነገሮች ሁሉ ማሰሪያ ነው፡፡ ስለሆነም በግብጽ የታየው ለውጥ እንኳን ደህና መጣህ የሚባል ቢሆንም የራሱ የሆኑ ተግዳህሮቶችም አሉት፡፡ ዋናው ነገር ደ/ር ዳኛቸው አሰፋ በአንድ ወቅት በሸገር ሬዲዮ እንዳሉት “ብርሐንን ስታይ ተከተል፡፡ ነገር ግን ወደ ሌላ ጨለማ እንዳያስገባህ ተጠንቀቅ” የዚህ ጽሁፍ መልዕክት ነው፡፡

Advertisements

የግብጽ ህዝባዊ መፈንቅለ-መንግስት እና የናይል ውሃ ጉዳይ፡ ከሞርሲ በኋላስ? (ክፍል አንድ)

ዘሪሁን አበበ ይግዛው

መንደርደሪያ

ታማሮድ ማለት በአረብኛ አማጺ ማለት ነው፡፡ እንደ አገባቡ የሚለያይ ቢሆንም ዋና መለያው ግን እምቢ ባይነት ወይም አልገዛም ባይነት ነው፡፡ ይህን ቃል በተደጋጋሚ የሰማነው ከሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ግብጽ ጋር ተያይዞ ነው፡፡ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየካቲት 25 ቀን 2011 የግብጹ ሆስኒ ሙባርክን ከመንበረ ስልጣናቸው ወደ ወህኒ ያዛወረው የታህሪር (የነጻነት) አደባባይ ትዕይንት ለግብጽ ታላቅ የዲሞክራ ብስራት እንደሆነ ብዙ ተነግሮለት ነበር፡፡ ይህ ብስራትም ጽንፈኛ ኢስላማዊ ነው ከሚባለው የሙስሊም ወንድማማቾች የተገኙትን ሞሐመድ ሞርሲን ወደ ስልጣን አመጣ፡፡ እጅግ ጠባብ በሆነ የድምጽ ቆጠራ ልዩነት የሆስኒ ሙባረክ መንግስት ባለስልጣን የነበሩትን አህመድ ሻፊቅን አሸንፈው ወደ ስልጣን የወጡት ሞርሲ ለሁሉም ህዝባቸው መሪ እና አስተዳዳሪ እንደሚሆኑ ቃል ገቡ፡፡ ይህም ታላቅ ብስራት ሆነ፡፡ ነገር ግን ይህ ብስራት ወደ ስብራትነት ሲቀየር ብዙም አልቆየም፡፡ ሞርሲ በግብጽ ታሪክ አይነኬ ነው፣ ነጻ ነው የሚባለውን የፍትህ አካል ነቀነቁ፡፡ ፕሬዝዳታዊ አዋጅ ብለው ራሳቸውን ከህግ በላይ ሹመው ቁጭ አሉ፡፡ አያያዛቸውም አዲስ ፈርኦን እሰኪመስል ድረስ፡፡ ለምን ይህን እንዳደረጉ ሲተቹም ህዝባቸውን በየካተት 25 ቀን ያገኘነውን አብዮት ለመጠበቅ እ ዳር ለማድረስ ነው አሉ፡፡ ቀጠሉ የፓርላማ ምርጫ ተካሄደ የእሳቸው ፓርቲ የፍትህ እና ሰላም ፓርቲ እንዲሁም መሰላቸው የሆነው እና ራሱን የእውነትፓርቲ-አል ኑር ብሎ የሚጠራ ቡድን የህግ ማውጫ ምክርቤቱን ብዙውን መቀመጫ ያዙ፡፡ ከዛም በግብጽ በሽምጥ ለኢስላማዊ መንግስት ማቋቋም መሰረት የሚሆን ህገ-መንግስት ማሯሯጥ ጀመሩ፡፡ የሀገሪቱ ሊበራል እና ለዘብተኛ ፓርቲዎች እንዲሁም የሀገሪቱ የክርስቲያኖች ተወካዮች ራሳቸውን ከህገ-መንግስት ማርቀቅ ሂደት አገለሉ፡፡ ሞርሲም በውድቀት ቁልቁለት የሚምዘገዘገውን ኢኮኖሚ ከማዳን ይልቅ በዚህ ስራ ተጠመዱ፡፡ ከዛም ታማሮድ ብሎ ራሱን የሰየመው ቡድን ፕሬዝዳንት ሞርሲ የስልጣናቸወን አንደኛ ዓመት በሚያከብሩበት በሰኔ 30 ቀን 2013 እንገናኝ ሲል ዛተ፡፡ የተቃዋሚ ፕርቲዎችንም ድጋፍ አገኘ፡፡ ሰልፍም ጠራ፡፡ ሞርሲንም ከስልጣን ይልቀቁ አለ፡፡ እሳቸውም እምቢ አሉ፡፡ የህዝቡን ልብ ለማማለል እና እንዲሁም የህዝባቸውን ቀልብ በአንድ ዋርካ ለመሰብሰብ በሚል እሳቤ ስለ አባይ ውሃ ዲሰኩር አበዙ፡፡ የጦርነትም ዳንኪራ መቱም አስመቱም፡፡ ዓለም ጉድ እያለ በቴሌቪዥን ተለፈፈ፡፡ ቀጥሎም ሞሐመድ ሞርሲ በናይል ውሃ ጉዳይ “ስለ አንድ ውሃ ጠብታ መቅረት ደማችን ለውጥ ይሆናል” አሉ፡፡ አስባሉም፡፡ ነገር ግን የቀድሞው ፕሬዝዳንት እንዳሰቡት አልሆነም፡፡ እንዲያውም ከወትሮው በተለየ ግብጻውያን በአባይ ጉዳይ ለየት ያለ አሳባቸውን ማስነበብ ጀመሩ፡፡ የሰለፉ ቀንም ደረሰ፡፡ ታማሮድ መራሹ ህዝብም የነጻነት አደባባይ ላይ ነጻነቴን ሲል ወጣባቸው፡፡ እሳቸው ግን አሻፈረኝ አሉ፡፡ በመሐልም በራሳቸው በሞርሲ ወደ መከላከያ ሚኒስትርነት ያደጉት ጄኔራል አብድል ፋታህ አል ሲሲም ለ “አለቃቸው” እንዲለቁ የጊዜ ገደብ ሰጧቸው፡፡ ሞርሲም “በመቃብሬ ላይ” አሉ፡፡ የሆኖ ሆኖ ሞርሲ ስልጣናቸውን በኃይል ለቀቁ፡፡ አዲስ የሽግግር መንግስትመ ተቋቋመ፡፡ ጥያቄው እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ባለበት ሁኔታ የሞሐመድ ሞርሲ ስልጣን መልቀቅ፣ የአዲስ መንግስት መመስረትስ ለአባይ ውሃ ፖለቲካ ምን ፋይዳ አለው… የሚል ይሆናል፡፡ ከዛ በፊት ግን ጥቂት ስለ መሐመድ ሞርሲ መንግስት እና ስለ ናይል አቋሙ እናወሳለን፡፡

የሞሐመድ ሞርሲ መንግስት እና የናይል ውሃ ፖለቲካ

የቀድሞ ተዋጊ ጄቶች አብራሪ፣ የዮም ኪፑር ጦርነት ዝነኛ፣ በኋላም ለ30 ዓመታት ግብጽን በፈርኦንነት የመሩት ሆስኒ ሙባርክ በናይል ወነዝ ዙሪያ ሀገራቸውን በድለው ነበር ያፉት ከተፋሰሱ ሀገራት ግንኑነት ጋር በተያያዘ፡፡ ምንም እንኳን የግብጽ የህይወት ውሃ ምንጪ አፍሪካ ብትሆንም ሆስኒ ሙባርክ ግን በመካከለኛው ምስራቅ ፖለቲካ ተወጥረው፣ ከምዕራባውያን ጋር ሲሻረኩ ወደ አፍሪካ አቅንተው አያውቁም ነበር፡፡ በተለይ በ1995በአዲስ አበባ በሱዳን ተቀነባበረ በተባለ የግድያ ሙከራ ከተደረገባቸው ወዲህ በአንዱምየአፍሪካ አንድነት ድርጅትም ይሁን የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ተሳትፈው አያውቁም ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ወደ ፕሬዝዳነትነት መንበር ካስጠጓቸው የቀድሞው ሟች ፕሬዝዳንት ሞሀመድ አንዋር አል ሳዳት የወረሱትን ማቀጠልን ከጀሉ ከአባይ አንጻር፡፡ ይህም ፉከራ እና ቀረርቶ እንዲሁም ከእኔ በላይ ላሳር ባይነት ሆነ፡፡ በመወያየት እ በመደራደር ደህና የሚባሉትን ለረጅም ጊዜ በውሃ ሀብት ልማት ሚኒሰትርነት የቆዩትን ደ/ር ሞሐመድ አቡ ዛይድ አንስተው  እጅግ ትምክህተኝነት እና ማንአለብኝነት የሚስተዋልባቸውን ደ/ር ሞሐመድ ነስር አልዲን ዓላምን ወደ ሚኒሰትር መስሪያ ቤቱ ቁንጮነት አመጡ፡፡ እናም በሳቸው ዘመን ከ10 ዓመታት በላይ በድርድር ያለፈው የቆየው የናይል ትብብር ስምምነት ማዕቀፍ (ናትስማ) የመቋጨት መንገድን ሰነቀ፡፡ ከሆስኒ ሙባርክ ከስልጣን መውረድ ቀደም ብሎም በግንቦት 2010 አምስት ሀገራት ናትስማን በኢንቴቤ-ዩጋንዳ ተፈራረሙ፡፡ የፊርማውንም ስርዓት ለተፋሰሱ ሀገራት ለ1 ዓመት ክፍት አደረጉ፡፡ በየካቲት 2011ም ሙባርክ በታህሪር ዓመጽ ስልጣነቸውን ለቀቁ፡፡ ቡሩንዲም ናትስማን በየካቲት 2011 ፈረመች፡፡ ይህ በመሆኑም የናትስማ አንቀጽ 42 እንዳስቀመጠው ፈራሚዎቹ ስድስት ሀገራት ስለሞሉ ህግ ለማድረግ ወደ ማጽደቅ ስራ መግባት ግድ ነበር፡፡ በመሐልም የግብጽ የህዝባዊ ዲፕሎማሲ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ እና ዩጋንዳ በማቅናት በግብጽ በተከሰተው የመንግስት ለውጥ እና አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ የፈራሚ ሀገራቱ  የማጽደቅ ያዘገዩ ዘንድ ጠየቁ፡፡ አዲስ ህዝባዊ መሰረት ያለው መንግስት ሲቋቋምም ግብጽ አቋሟ እንደሚቀየር እንደበፊቱ (እንደ ሙባርክ መንግስት እንደማይሆን) ገለጹ፡፡ እንዳሉትም ሆነ፡፡ በመሐል የነበረው እና በኤሳም ሻራፍ የሚራው የሽግግር መንግስትም የሙባርክ ዘመን አካሂያድ እንደማይደገም ገለጹ፡፡ አዲስ መንግስትም ሞሐመድ ሞርሲን በሰኔ 30 ቀን 2012 ወደ ስልጣን አመጣ፡፡ ከዛስ…. ?

ምንም አንኳን አዲስ መንግስት ይቋቋም እንጅ የግብጽ መሰረታዊ የናይል ፖሊሲ ሳይቀየር እንደነበረ ቀጠለ፡፡ ምንም እንኳን የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት የግብጽን ወቅታዊ ሁኔታ በማተዋል የህዝባዊ ዲፕሎማ ቡድኑ ያቀረበውን ጥያቔ ቢቀበሉም የሞሀመድ ሞርሲ መንግስት ምላሽ ግን እጅጉን አሳዛኝ እና አበሳጭ ነበር ለላይኛው ተፋሰስ ሀገራት፡፡ በዋናነት ሁለት ጉዳዮች ነበሩ የአባይ ተፋሰስ የፖለቲካ ሞቅታ መነሾዎች፡፡ አንደኛው የናትስማ ጉዳይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የታላቁ የኢትዮያ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ ናቸው፡፡ የሞርሲ መንግስት ፖሊሲ ከእነዚህ ጉዳዮች አንጻር ምን ይመስል ነበር ብለን ስንጠይቅ እንደሚከተለው ሆኖ እናገኛለን፡፡

የሞርሲ መንግስትና የናይል ትብብር ስምምነት ማዕቀፍ (ናትስማ) 

የግብጽ የናይል ፖለሲ የሚያጠነጥነው ማንንም በማያስገባ ያረጀ አጥር ውስጥ በሚሽከረከር እና ለራስም በማይበጅ አኳኋን የተቀመረ ነው፡፡ ለግብጽ የ1959 የሁለትዮሽ (ግብጽ እና ሱዳን) ስምምነት አይነኬ እና አይደፈሬ ነው፡፡ ስለሆነም ማንኛውም የአባይ ስምምነት ከወጣ ሲወጣ ይህን ስምምነት የተቀበለ እና ያጸደቀ መሆን አለበት ለግብጽ፡፡ ይህ ስምምነት በዋናነት ዓመታዊውን የናይልን ውሃ ፍሰት (84.1 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር)ሙሉ በሙሉ ለግብጽ፣ ለሱዳን እና ለትነት ከማከፋፈሉ በተጨማሪ በዓለምአቀፍ የውሃ ህግ ምንም ዓይነት ተቀባይነት የሌላቸው እና ያረጁ የውሃ መሰረተ-አምነቶችን (ታሪካዊ መብት ወይም የቀደመ ተጠቃሚ የቀደመ ባለመብት) ብሎ በመደንገግ ግብጽን የናይል ተፋሰስ ፈላጭ ቆራጭ አድርጎ ሰይሟል፡፡ ነገር ግን እንኳን ያልፈረሙት እና የማያውቁት ኢትዮጵያና ሊሎች የራስጌ ሀገራት ፈራሚዋ ሱዳን እንኳን ኩርፊያዋ እጅግ የበዛ ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ይህ ስምምነትም ሆነ ለዚህ ስምምነት መንደርደሪያ የሆነው የ1929 የቅኝ ግዛት ስምምነት በራስጌ ሀገራት ተቀባይነት የሌላቸው ሲሆን ሀገራቱ በናትስማ በኩል ዓለምአቀፋዊ ቅቡልነት ያላቸውን የፍትሐዊ እና ምክኒያታዊ አጠቃቀም መርህን እንዲሁም በዚሁ ስር በሌለች ተፋሰስ ሀገራት ላይ የጎላ ጉዳት ያለማድረስ መርሖወችን በመደንገግ ውድቅ አድርገውታል፡፡ ይሁን እንጅ ግብጽ ይህን ስምምነት በመፈረም በናይል ላይ እኩል ተጠቃሚነትን ከማፈን ይልቅ ይህን ስምምነት ከግቡ እንዳይደረስ ለማድረግ ሌት ተቀን መስራቱን ተያያዘችው፡፡ በሙባርክ መነግስትም ጊዜ ሆነ በሞርሲ መንግስት የሆነው ይህ ነው፡፡ የናትስማ ፈራሚ ሀገራትን ለመከፋፈል በመሞከር ስምምነቱ እንዳይጸድቅ ለማድረግ ነበር የተሞከረው፡፡ በግብጽ ፖሊሲ አውጪዎች በኩል ትኩረት የተሰጠውም የተፋሰስ-ዓቀፍ ትብብር ጉዞ ሳይሆን የሁለትዮሽ ትብብር ነበር፡፡ ይህም ግብጽ አንዱን ሀገር ካንዱ ለመነጠል ያደረገችው እንቅስቃሴ አካል ነው፡፡ ለዝርዝሩ ይህችን ይጫኑ፡፡ ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ ናትስማን ህግ አድርጋ ያጸደቀች ሲሆን ዩጋንዳም ሂደቱን ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ ይህም የግብጽ ከፋፍለህ ግዛ አካሄድ ያለመሳካቱን ብቸኛው መፍትሔ ስምምነቱን ተቀብሎ የናይል ተፋሰስ ኮሚሽንን ማቋቋም እንደሆነ ይነግረናል፡፡ ይሁን እንጅ የሞርሲ መንግስት በቆየባቸው 12 ወራት ናትስማን ዘወር ብሎለማየት አለመሞከሩ እና የሙባራክን ውርስ ይዞ መቀጠሉ ያለንም እኛው የወረድንም እኛው የሚያብስል ነው፡፡

የሞርሲ መንግስትና የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ፡ ከጉደኛው የቴሌቪዥን ስርጭት እስከ ደማችን አማራጭ ነው

ኢትዮጵያ የህዳሴው ግድብ መገደብ ከጀመረች እነሆ ሁለት ዓመት ተቆጠረ፡፡ ግብጽ ይህ ግድ ባይዋጥላትም እውነታ ነውና እውነታውን መቀበል ግን የግድ እንደሆነ የተረዳች ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያ ግድቡን የምትገነባው መብቷ በመሆኑና የሕዝቧንም ፍላጎት ለማሟላት እንደሆነ ብትገልጽም ለግብጽ አልተዋጠላትም፡፡ ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን በዚህ ግዙፍ ፕሮጀክት እምነት እንዲኖራቸው፣ ጥቅሙም ለጋራ ለተፋሰሱ ሀገራት ጭምር እንጅ ለኢትዮጰያ ብቻ የተወሰነ እንዳይደለ ለማስረዳ በራሷ ተነሳሽነት እና ውሳኔ ከሶስቱ ሀገራ የጠወጣጡ ስድስት እንዲሁም አራት ዓለምአቀፍ ባለሙያዎችን የያዘ የባለሙያዎች ቡድን እንዲቋቋም በማድረግ የግድቡ ጥቅም እንዲታይ ያልታየ ጉዳትም ካለ እንዲጠና አደረገች፡፡  የባለሙያዎች ቡድኑም የደረሰበትን የመጨረሻ ሪፖርት እና የጥናት ውጤት ለሶስቱ ሀገራት መንግስታት በሰኔ 1 ቀን 2013 አስረከቡ፡፡ ከዚህ 3 ቀናት ቀደም  ብሎ በግንቦት 28 ቀን 2013 ኢትዮጵያ የግድቡን ዋና አካል ግንባታ ለማከናወን ያስችል ዘንድ የአባይን ውሃ በ500 ሜትር አቅጣጫ ማቀየሯን ይፋ አደረገች፡፡ በዚህ መሐል ከወደ ግብጽ የተሰማው መልስ ግን በጣም የተሟሟቀ ነበር፡፡ አንደኛ የወንዙ አቅጣጫ መቀየር ወደ ሌላ ቦታ መጠለፍ ሆኖ በዜና ማሰራጫወች በመነዛቱ ለግብጻውያን ትልቅ ዱብእዳ ነበር፡፡ ይህም የፖለቲካ ፓርቲ መረዊችንም ጭምር ክፉ እና ደግ እንዲናገሩ አደረገ፡፡ ሁለተኛ የባለሙያዎች ቡድኑ ላቀረበው ሪፖርት ከግብጽ መንግስት (ከመሐመድ ሞርሲ) የወጣው መልስ የችኮላ እና በቀደመ አዕምሮ እና ፖሊሲ የታጠረ ነበር፡፡ ይህም ግድቡ የግብጽን የውሃ ደህንነት ይጎዳል ስለሆነም አደጋ ላይ ነን የሚል ዓይነት መልስ ተበተነ፡፡ በዚህም ምክንያት ጩኸቱ በርከትከት ሲል ፕሬዝዳንት ሞርሲ ጥሩ ከውስጥ ፖለቲካ ማስቀየሻ አጋጣሚ ያገኙ ስለመሰላቸው ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች ኑ ስለ ሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም እናውራ ብለዉ ጋበዙ፡፡ ዋና ዋናዎች ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች (ሞሐመድ አልባራዳይ፣ አመር ሙሳ እና ሐመዲን ሳባሂ) ባይገኙም የሳላፊስቶቹ አል ኑርን ጨምሮ ሌሎች ተገኙ፡፡ በዚህ ብሔራዊ ውይይት በተባለው እና በፕሬዝዳንቱ ቢሮ በተሰናዳው ትዕይንት ግብጽን ከውስጥም ከውጭም ያስነወረ ድርጊት ተፈጸመ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች ያደረጉት ንግግር በቀጥታ ቴሌቪዥን ሲተላለፍ መሪዎቹ ኢትዮጵያን ከታላቁ ህዳ ግንባታ ለማስቆም ከተራ ስፖርተኞቻችንን እና አርቲስቶቻችንን እስከ የእንዲህ ዓይነት የጦር መሳሪያ አለን የውሸት ወሬ እንዲሁም ጸረ-የኢትዮጵያ መንግስት ኃይሎችን እንጠቀም የሚሉ ንግግሮችን ዓለም ሰማም አየም፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ስለ ሀገራቸው የናይል ተፋሰስ ሀገራትን ይቅርታ የጠየቁት በቦታው ያልነበሩት የተቃዋሚ መሪው ሞሀመድ አልበራዳይ ብቻ ነበሩ፡፡ ይህን ተከትሎ ከቀናት በኋላ በዋናነት የግብጽ ኢስላማዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰባስበው ባዘጋጁት የፕሬዝዳንቱ የናይል ንግግር ላይ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሞርሲ ስለ ደም እንዳወሩ ንግግሩን ጨረሱት፡፡ ናይልን በተመለከተ ሁሉም አማራጮች በጠረጴዛ ላይ ናቸው በማለት በተዘዋዋሪ የጦርነት ታምቡርን አጩኸው ነበር ሞርሲ፡፡ በማስከተልም  አንዲት ጠብታ ውሃ ብትቀንስ ደማችን አማራጭ ነው ያሉት ሞርሲ በርግጥም በውስጥ የተቀሰቀሰባቸውን የፖለቲካ ተቃውሞ ለማምለጥ የተጠቀሙበት እንደነበር ግብጽ በዚህ ሰዓት መዋሀድ እና አንድ መሆን አለባት ሲሉ በንግግራቸው መማጸናቸው ያሳጣባቸዋል፡፡ 

የሆኖ ሆኖ ደም ደም ለሸተተው የፕሬዝዳንቱ ንግግርም ሆነ ለፖለቲካ ፓርቲዎቹ ለብጥብጥ የሚጋብዝ ንግግር በኢትዮጵያ የተወሰደው የትዕግስት እርምጃ እና ሉዓላዊነትን ያስጠበቀ እና ጥንቃቄ የተሞላበት መልስ የሚደነቅ  ነበር፡፡ ከሞርሲ መንግስት የምንረዳው ዋና ነገር ቢኖር ከናይል ውሃ አንጻር ምንም ዓይነት የጸባይም ሆነ የባህሪ ለውጥ ያመጣ መንግስት አለመሆኑን ነው፡፡ የጦርነት ዛቻዎቹም ሆነ ቀረርቶዎቹ ከሞሀመድ አንዋር አል ሳዳት ጀምሮ በሞሐመድ ሆስኒ ኤል-ሰይድ ሙባርክ በኩል ለሞሐመድ ሞሐመድ ሞርሲ ኢሳ አያት የደረሰ ነው፡፡ ሳዳት በ1979 ግብጽን ወደ ጦርነት የሚወስዳት ብቸኛ ነገር ቢኖር ውሃ ነው ብለው ለፈፉ፡፡ ተከታያቸው ሆስኒ ሙባርክም በበ1990ዎቹ አጋማሽ ሱዳንን በናይል ውሃ ጉደይ አስጠነቀቁ በቦምብ እናወድማችኋለን በሚል እሳቤ፡፡  በሙባርክ ዘመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አመር ሙሳም ሱዳንን በእስትም በውሃም አትጫወች ሲሉ አስጠነቀቁ፡፡ ኢትዮጵያንም በተመለከተም እኒሁ ሰው ለኢትዮጵያ በጎ ምኞት አለን መብታችንን እስካልነካች ድረስ ብለው በወቅቱ ለሚታተመው እፍይታ መጽሄት በገደምዳሜ ማስጠንቀቂያቸውን አስተላለፉ፡፡ እነዚህ ምስሎች በጥቅሉ የሚነግሩን የጦርነት ታምቡሮቹ የቆዩ እና የነበሩ እንዲሁም ሞርሲም የወረሷቸው መሆናቸውን ነው፡፡ ይንም ውርስ ሞርሲ የውስጥ ፖለቲካቸውን ለማደፈን በአርበኝነት ስሜት ደማችን ጠብ ይላል ሲሉ ተደመጡ፡፡

 ይሁን እና ሞርሲም ያሰቡት ሳይሳካ የታህሪር ቀጠሮ ደረሰ ሰኔ 30 ቀን 2013፡፡ በሀገሪቱ ጦር ሰራዊት የተሰጣቸውን ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ተነጋግረህ የሀገሪቱን ቀውስ ፍታ የሚል የ48 ሰዓት የጊዜ ገደብ በማሳለፋቸው ሞርሲም በታህሪር ጩኸት በታንክ ግፊት ቤተ መንግሰቱን ለቀቁ፡፡ የሀገሪቱ ሰራዊት የበላይ የሆኑት ጄኔራል አል ሲሲ አዲስ ሀገሪቱን ያረጋጋል እንዲሁም ለመጪዋ ግብጽ መንገድ ይጠርጋል ያሉትን እና በሼኩም በፓትርያረኩም የተባረከ ቀያሽ-እቅድ/ትልመ-ግብ/road-map አዘጋጁ፡፡ በመሆኑም በጽንፈኞቹ በሩጫ የተሰናዳው ህገ-መንግስትም በአጭር ተቀጨ፡፡ አዲስ የሽግግር መንግስትም ተቋቋመ፡፡  ጄኔራል አል ሲሲ የሀገሪቱ የፍትህ አካል የበላይ ዳኛ የሀገሪቱ የሽግግር ፕሬዝዳንት ሆነው መሾማቸውን አወጁ፡፡ ህግ-አውጭው ምክርቤት/ሹራ ጉባኤም በአዲሱ ፕሬዝዳንት ተበተነ፡፡ አዲስ ጠቅላይ ሚኒሰትር ሀዜም ኤል ባብላዊም በሽግግሩ ፕሬዝዳንት ተሾሙ፡፡ እሳቸውም የሽግግር መንግሰቱን ከባለሙያወች አውጣጥተው ካቢኒያቸውን በመሰረት ላይ ይገኛሉ፡፡ የሞርሲ መንግስት በዋናነት መወገድ እንዲሁም ይህ የሽግግር መንግስት መመስረት ከናይል ተፋሰስ አንጻር ምን አንድምታ ሊኖረው ይችላል የሚሉትን ሀሳቦች በሚቀጥለው እትም እንጎበኛለን፡፡ 

ይቀጥላል