የሞርሲ መንግስት መወገድ፡ ዕድል እና ተግዳህሮቶች (ክፍል ሁለት)

ዘሪሁን አበበ ይግዛው

በመጀመሪያው ክፍል የግብጽ ህዝባዊ መፈንቅለ-መንግስት እና የናይል ውሃ ጉዳይ፡ ከሞርሲ በኋላስ? በሚል ርዕስ በዋናነት የሞርሲ መንግስት የአባይ ፖሊስ በመሰረቱ የቀደመውን እና ከሙባርክም ሆነ ከሙባርክ በፊት የነበረን የግብጽ ግትር የናይል ፖሊሲ እንዲሁም ዛቻ እያይዞ የቀጠለ መሆኑን ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ በዚህ ክፍል ደግሞ ሁለት አበይት ጉዳዮች ላይ ወፍ በረር ቅኝት እናደርጋለን፡፡ አንደኛው የሞርሲ መንግስት መውደቅ ያለው በጎ አስተዋጽኦ ከናይል ተፋስ አንጻር ሲሆን ሁለተኛው የሞርሲን መንግስት ተከትሎ ስለመጣው የሽግግር መንግስት ሁኔታ ዕድሎችን እና ተግዳህሮቶችን እንቃኛለን፡፡ ሆኖም በመሐል በሞርሲ አስተዳደር ዘመን ስለነበረው የድርድር ጅማሮ ይጠቀሳል፡፡

የፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሞርሲ መወገድ ለግብጽ በዋናነት በመቀጠል ለምስራቅ አፍሪካ እና መካከለኛው ምስራቅ በጎነት በውስጡ ይዟል፡፡ ማን እንደሚመራቸው የሚውስኑት ግብጻውያ ራሳቸው ናቸው፡፡ ሆኖም ግን በበርም ይን በጓዳ ይግባ ሀገሪቱን የሚመራ/በአገዛዝ ወንበር ላይ ያለ አካል በአንድም በሌላም መልኩ የሚከተለው የውጭ ግንኙነት እና ዓለምአቀፍ ፖለቲካ አመለካከት የሚመለከታቸው ሀገራት ስላሉ ነገሩን ከዚሁ አንጻር አስተያየት መስጠት ተገቢ ይመስለናል፡፡ ስለሆነም ለ80 ዓመታት አንድ እባብ እናት እናቱን እየተባለ ያልጠፋው የሙስሊም ወንድማማቾች በግብጽ ወደስልጣን ብቅ ማለት በአንድም በሌላም መልኩ የግብጽ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ላይ ለአንድ ዓመትም ቢሆን አሻራውን ጥሎ አልፏል፡፡ ከዚህ አንጻር የአባይ/የናይል ውሃ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ የሞርሲ መንግስት በመጀመሪያው ክፍል አንደተዳሰሰው ያለአግባብ እና ትምክህተኝነት እና የማይበጅ ማንአለብኝነትን ገሀድ ባወጣ መልኩ የተሰሙት ተደጋጋሚ ዲስኩሮች በአንድም በሌላም መልኩ የግብጽን ከናይል ተፋሰስ ሀገራት ጋር የሚኖር ግንኙነት እጅጉን ሸካራ ያደርግ ነበር፡፡ በተለይ ፕሬዝዳንቱ እና መንግስታቸው የአገዛዙን መንበር እንደያዙ ቀጥሎ ቢሆን ኖሮ ትንሽ ጉዳቱ ከፍ ይል ነበር፡፡ ይህም በዋናነት ሁለት መሰረታዊ ነገሮች ላይ የቆመ ነበር፡፡ አንደኛው የህግ አውጭወን አካል ከተቆጣጠሩት ፓርቲዎች አንጻር የሚመነጭ ሲሆን ሁለተኛው እና ተያያዡ ጉዳይ እነዚህ ፓርቲዎች ያላቸው ንጽሮተ-ዓለም ነው፡፡ ይህን የምናነሳባት ዋናው ጉዳይ ህግ-አውጭው አካል የስራ አስፋጻሚውን ተጽእኖ ባንድም በሌላ መልኩም ስለሚያሳድር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ስናይ የግብጽ የላይኛው ምክር ቤት በዋናነት ካሉት 180 መቀመጫዎች ውስጥ ብዙውን ኢስላማዊ አክራሪነትን በሚያራግቡት የሙስሊም ወንድማማቾቹ የሰላም እና ፍትሕ ፓርቲ (106) እንዲሁም የሰላፊያው ቡድን ፓርቲ አል-ኑር (46) የተያዘ ነበር፡፡ የአክራሪነት አጀንዳ በገሀድ የሚያጸባርቁት እነዚህ አካላት ያላቸው ንጽሮተ-ዓለምም የተንሸዋረረ እና በዚሁ መስመራቸው የተቃኘ  ነው፡፡ ለምሳሌ ያክል ከቤተ-መንግስት በቀጥታ በስህተትም ሆነ ታስቦበት በተላለፈው ውይይት ላይ እነዚህን ነገሮች እናስተውላለን፡፡  ከናይል ወንዝ አንጻር እንግዲህ ሰላማዊ መንገድን አንከተላለን ስላሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሂሻም ቀንዲል በዚህ ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ ሲሰጡ መወረፋቸውን ማስታውስ ግድ ይሏል፡፡

ከዚሁ ከንጽሮተ-ዓለም ጋር በተያያዘ የምናገኘው ሌላኛው ጉዳይ የእነዚህ ፓርቲዎች ያላቸው ወይም የለመደባቸው እስራኤልን እና የናይልን ውሃ የማተሳሰር ነገር ነው፡፡ ይህንም በቀጥታ በተላለፈው ውይይት ላይ ሲጠቀስ እንሰማለን በአል-ኑር ፓርቲው ሊቀመንበር ዛካሪያ ዩኑስ አበድል-ሃሊም ማክዮን፣ በአል-አዘሃሩ ሼክ ሀሰን አል-ሻኤፍ እንዲሁም የኢስላሚክ ሌበር ፓርቲው ማግዲ አህመድ ሁሴን:: በሌላም መልኩ የእነዚህ ኃይሎች የምስራቅ አፍሪካ የሚያዩበት መነጽር እንዲሁ የተንሸዋረረ ለመሆኑ ማሳያ በተለያያ ጊዜ የሙስሊም ወንድማማቾች በእንግሊዘኛ ድረ-ገጹ ያወጣቸውን ጽሁፎች መመልከቱ ጠቋሚ ነው፡፡ የሙስሊም ወንድማማቾች በሱዳንም እንዳለ ሁሉ በሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮችም እንዲስፋፋ ፍላጎቱ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ በ2006 እኤአ ወደ ሶማሊያ መግባት ተከትሎም የሙስሊም ወንድማቾች ለሶማሊያው ኢስላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት አጋዥ የሆነ መግለጫ ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ በጥቅሉ እጅጉን ባህልን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ ሌላ ግጭት ወይም የጥቅም ፉክክር ሊነሳ እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡ ከዚሁ ጋር የሚያያዘው በኢትዮጵያ እግሩን እና እጁን ብቅ ብቅ እያደረገ ያለው የሳላፊያ እንቅስቃሴም ለዚሁ ዓላማ መጠቀሚያ ፈረስነት አያመልጥም ነበር፡፡ በሀሰን አልቱራቢ በሱዳን እንዲሁም በደ/ር አሊ ባሻ በሶማሊያ የሚመሩትን ሙስሊም ወንድማማቾች  ስናስብ የሚሰጠን የራሱ የሆነ ምስል አለ፡፡ በተጨማሪም ከአሁን በፊት እንደጠቀስሁትም የቱርክ የሶማሊያ እንቅስቃሴም ከዚሁ አንጻር የሚታይ ነው፡፡ ያለነገርም እኮ አይደለም የቱርኩ ጠቅላይ ሚኒስትር ጠይብ ኤርዶጋን ሞሐመድ ሞርሲ ፕሬዝዳቴ ነው ያሉት፡፡  ይህ ሁሉ ነገር ተደምሮ ለናይል ውሃ ድርድር እንቅፋት መሆኑ አይቀሬ ነበር፡፡ ይህ ማለት ግን የአክራሪነት አጀንዳ ያላቸው የእነ ሞርሲ መንግስትነት አክትሟልና ከተግዳሮት ነጻ የሆነ መወያያ መድረክ ተፈጥሯል ማለትም አይደለም፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ነገር ቢኖር የሞርሲ መንግስት የቅርብ እረዳት እና አጎብዳጅ የነበረው አጅግ አክራሪው የሰለፊያው አል-ኑር ፓርቲ የፖለቲካ እክሮባቱን በማጠንከር ከሽግግር መንግሰቱን ተቀብሏል፡፡ ዞሮ ዞሮ በሚደረግ ምርጫ እነዚህ ቡድኖች ተመልሰው ወደ ስልጣን ከመጡ የተፈራው ነገር መመለሱ አይቀርም፡፡ ስለዚህም ይህን እያሰቡ መራመድ አስተዋይነት ነው፡፡  ምንግዜም ቢሆን በወሰን ተሸጋሪ ወንዞች ላይ በሀገራት መካከል የሚደረጉ ድርድሮች እና ውይይቶች በውሃ ፖለቲካ ታሪክ፣ የአቅም ሚዛን፣ ኢኮኖሚ እና ወታደራ ኃይል፣ መልከአ-ምድር፣ ሐይማኖት እና ባህል፣ ንግድ፣ የመንግስታት/አገዛዝ ዓይቶች እና ባህሪ ወዘተ ጥላ ለበጎም ለክፉም የሚያርፍባቸው ናቸው፡፡ ስለሆነም የሙስሊም ወንድማማቾች በዚህ ሰዓት ከፖለቲካው ዋና ተዋናይነት ገለል ማለት የራሱ የሆነ በጎ ገጽታ እንዳለው እንረዳለን፡፡

በሌላ መልኩ በሙርሲ ይመራ የነበረው መንግስት መወገድ በራሱ ተግዳህሮቶችን ይዞ መምጣቱ አልቀረም፡፡ በሞርሲ መንግስት አስተዳደር ውስጥ በአባይ ውሃ ጉዳይ ላይ አራት ቁልፍ ሰዎችን እናስተውላለን፡፡ አንደኛ ፕሬዝዳንቱ፣ ሁለተኛ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሶስተኛ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እንዲሁም አራተኛ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ በናይል ውሃ ጉዳይ ላይ በተደጋጋሚ እነዚህን ሰዎች እናውቃቸዋለን፡፡ በተለይ የውሃ እ መስኖ ሚኒስትሩ ሞሐመድ ባሐ ኤል-ዲን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሞሐመድ ካሜል አምር፡፡ ነገሮች ጡዘው በነበሩነት እና የቀድው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ ሞርሲ የውስጥ ጉዳያቸውን ወደ ውጭ ለማቀየስ በጣሩበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ከኢትዮያው አቻቸው ደ/ር ቴድሮስ አዳህኖም ጋር ለድርድር የተቀመጡት ሞሐመድ ካሜል አምር የሞርሲን የመጨረሻ ንግግር ተከትሎ ስልጣናቸውን መለቀቃቸውን አሳውቀው ነበር፡፡ ሆኖም የሽግግር መንግስቱ እስኪሰየም ድረስ በመቆየት ለሽግግር መንግስቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነቢል ፋሚ አስረክበዋል፡፡ ምንግዜም ቢሆን የተረጋጋ መንግስት ከለለ እና ስራ አስፈጻሚዎቹ አካላት በተለያየ ምክንያት በተቀያየሩ ቁጥር በድርድር እና ውይይት የራሱ የሆነ ተጽእኖ አለው፡፡ ይህ የሞርሲ መንግስት ካቢኔ መፍረስ ያስከተለው አንድ ተግዳህሮት ነው፡፡ ድርድሩን የሚያካሂዱት አካላት ሰዎች እንደመሆናቸው መጠን ዕለት ዕለት በጉዳዩ ዙሪያ እየተገናኙ እን እያወሩ በመጡ ቁጥር ወዳጅነትም ጓደኝነትም ወንድማማችነትም ሊመሰረት ይችላል፡፡ ይህም በጎ የሆነ የድርድር መንፈስን እና መተማመንን ሊያመጣ እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

በዶ/ር ቴድሮስ እና በሞሐመድ ካሜል አምር መካከል የታየው በጎ የሆነ በህዳ ግድብ ዙሪያ ያለውን ችግር ለመፍታት የተደረገ የድርድር ሂደት በጎ ጎኖችን ይዞ ብቅ ማለቱ የሚታወስ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እና ግብጽም ሱዳንን በመጨመር የዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድኑ ባቀረበው ሀሳብ መነሻነት ድርድሩን እና ውይይቱን ለመቀጠል ተስማምተው ነበር የተለያዩት፡፡ በመሐል ግን የግብጽ ውስጣዊ የፖለቲካ ሁኔታ ባለመፍቀዱ ነገሮች እንደታሰበው አልሄዱም፡፡ የሆነ ሆኖ በግብጽ አዲሱ የሽግግር መንግስት አዲስ ፕሬዝዳንት አድሊ መንሱር፣ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር- ሀዜም ኤል-ቤብላዊ፣ አዲስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነቢል ፋሚ እንዲሁም አዲስ የመስኖ ሚኒስትር ሞሀመድ አበድለ ሙጣሊብን እንዲሁም መከላከያ ሚኒስትሩን ጄኔራል አበድል ፋታህ አል-ሲሲን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነትሞሐመድ አል-ባራዳይን ደግሞ የውጭ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት አድርጎ ይዟል፡፡ የእነዚህ ሰዎች ወደዚህ ቦታ መምጣት የራሱ የሆነ አንድምታ አለው፡፡

አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤብላዊ የመንግስታቸው አንዱ ትልቅ ስራ ኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ባለቸው የህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለ አለመግባባት በሰላማዊ መንገድ መፍታት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነቢል ፋሚም በመጀመሪያው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ኢትዮጵያን ከመምጣታቸው ስንጠራት አቤት አልለን አለች በሚል መንፈስ መክሰሳቸው ውይይቱን እና ድርድሩን በገንቢነት ከመቀጠል ይልቅ ወደ ኋላ ይጎትተዋል፡፡  የሆነ ሆኖ አዲሱ ውጭ ጉዳይ ሚኒትር አያይዘው አዲስ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ አፈሪካን እና ጎረቤት ሀገሮችን መሰረት በማድረግ እንደሚቀርጹ አስረድተዋል፡፡ ይህ ከሆስኒ ሙባርክ መንግስት ውድቀት ማግስት ጀምሮ በተደጋጋሚ የተለፈፈ ጉዳይ ቢሆንም ተግባራዊ ግን አልሆነም፡፡ ለምሳሌ ከሞርሲ መመረጥ በፊት የነበረው የኤሳም ሻራፍ የሽግግር መንግስት በመስከረም 2011 ኢትዮጵያ እና ግብጽ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ እንደሚከፍቱ ገልጸው ወደኋላ መመለስ እንደማይቻል እንዲሁም የቀደመው መንግስት የተሳሳተ ፖሊሲ ቀርጾ ይንቀሳቀስ እንደነበር አክለው ወደ ኋላ መመለስም እንደሌለ አስረድተው ነበር፡፡ ይሁን እና በአፍ የሚባለው ነገር ከሚደረገው ነገር ነገር ጋር ገጥሞ አልተስተዋለም፡፡ የሞርሲ መንግስትም እንዲሁ አስተጋቶ ነበር፡፡ ነገር ግን በተግባር የሆነው ያ ቀድሞ በሙባርክ እና ሳዳት ዘመን የነበረው የከፋፍለህ ግዛ እና የቀረርቶ ፖሊሲ ነበር፡፡

በእርግጥ አዲሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ይዘውት የመጡት ነገር ግብጽ የውሃ ዋስትና ፖሊሲዋን እንደገና መፈተሸ አለባት ማለታቸው ነው፡፡ በዚህም መሰረት የውሃ ዋስትና የሚለው ሐረግ አንድገና ትርጓሜ እንደሚያሻው ገልጸዋል፡፡ ምን ዓይነት የሚለው ግን ወደፊት የሚታይ ነው፡፡ ነገር ግን የውሃ ዋትናነት ከብሔራዊ ድህንነት ጉዳይ ጋር በማተሳሰር እና ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ፍቺ እንዲኖረው የሚደረግ ከሆነ ዞሮ ዞሮ እዚያው ነው የሚሆነው፡፡ የውሃ ዋስትና በመሰረቱ ከኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር እንዲሁም ውሃን ፍትሐዊ እና ምክንያዊ በሆነ መልኩ ከመጠቀም መርህ ጋር ተያይዞ ሲበየን ወይም ሲተረጎም የተፋሰሱን ሀገራት ወደ ሰላም እና ትብብር ይወስዳል፡፡ ሆኖም ግን ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ብያኔ ከተሰጠው ልዩነትን ማፋቱ በተግባር የታየ  ነው፡፡ ግብጽ ነቢል ፋሚ እንዳሉት የውሃ ዋስትና ጉዳይ እንደገና መመርመር ያለበት ይህም በጎ የሆነ አቀባበል የሚኖረው ነው፡፡ ሆኖኖም ግን ነቢል ፋሚ በ2011 ሚያዝያ ወር ላይ ስለ ናትስማ (የእንቴቤው ስምምነት) አስተያየት ሲሰጡ ይህ ስምምነት በመፈረሙ የናይል ተፋሰስ እንደ ቀድሞው አለመሆኑን ይናገረላ፡፡ ሆኖም ግን ነቢል ፋሚ የዚህን ስምምነት ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርህ ከመቀበል ይልቅ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ያላቸውን ብዙ ውሃ የሚያጠራቅሙበትን መንገድ መፈለግ አለብን ይላሉ፡፡ በዚሁ አስተያየታቸው ላይ የላይኛው ተፋሰስ የውሃ ፕሮጀክቶች ለኤሌከትሪክ ማመንጫ ይሁኑ እንጅ ዲዛይቻቸው ወደ ግብጽ ውሃ እንዳይሄድ ለማድረግ ወይም ለመቆጣጠር እንዲያች ተደርጎ ሊሰራ ይችላል ሲሉ የተሳሳተ ጥርጣሪያቸውን ይገልጻሉ፡፡ አለመተማመን እና ጥርጣሬ ካለ እንዴትስ ትብብር ሊመጣ ይችላል፡፡ የእኒህ ሰው አስተሳሰብ በመሰረቱ በካይሮ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ካሉት እንደ እን ሞሐመድ ነስር አል ዲን አላም የተለየ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ የሆነ ሆኖ የውሃ ዋስትናን እንዴት እንደሚተረጉሙ እንዲሁም ደግሞ በሀገራቱ መካከል በሚደረገው ድርድር ለውጦቹ የሚታዩ ይሆናል፡፡

ለማጠቃለል ያክል በወሰን ተሸጋሪ ወንዞች ዙሪያ በሚደረግ እሰጣ-ገባ ውስጥ አንዳንድ ጸብ-አጫሪነት የሚያጠቃቸው መሪዎች መወገዳቸው ለአጠቃላይ ተፋሰሱበጎ የሆነ አንደምታ ቢኖረውም የራ የሆኑ ተግዳሮቶችም አሉት፡፡ በዋናነትም ቶሎ ማለቅ የሚችልን የድርድር ሂደት ማራዘሙ የግድ ነውና፡፡ ውይይት እና ድርድር ሰዎችን መሰረት አድርጎ የሚካሄድ በመሆኑ በሰዎች መካካል በጎ የመግባባት እና የመወያየት መንፈሶች ሲኖሩ ድርድሩን ያግዛሉ፡፡ ምንም እንኳን በፊትም የነበሩም ሆነ ያልነበሩ ባለሙያዎች ፖለቲከኞችን ከጀርባ በመሆነ የሚያግዙ እና ዋናውን ስራ የሚሰሩ ቢሆንም በፖለቲከኞች መካከል ያለ ግንኙነት የነገሮች ሁሉ ማሳረጊያው ነው፡፡ ምንግዜም ቢሆን ሳይንስ እና ባለሙያዎች መደራደር እና መወያየት እንዳለ ቢያሳኑም፣ የተለያየ የመፍትሔ ሀሳብ ቢያቀርቡም የሀገራቱ የፖለቲካ ውሳኔ የነገሮች ሁሉ ማሰሪያ ነው፡፡ ስለሆነም በግብጽ የታየው ለውጥ እንኳን ደህና መጣህ የሚባል ቢሆንም የራሱ የሆኑ ተግዳህሮቶችም አሉት፡፡ ዋናው ነገር ደ/ር ዳኛቸው አሰፋ በአንድ ወቅት በሸገር ሬዲዮ እንዳሉት “ብርሐንን ስታይ ተከተል፡፡ ነገር ግን ወደ ሌላ ጨለማ እንዳያስገባህ ተጠንቀቅ” የዚህ ጽሁፍ መልዕክት ነው፡፡

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s