የግብጽ ረቂቅ ህገ-መንግስት እና የአባይ ውሃ ጉዳይ

በዘሪሁን አበበ ይግዛው

GERDየሆስኒ ሙባርክን በ2011 በህዝባዊ አመጽ ከሥልጣን መወገድ ተከትሎ ግብጽ የተለያዩ ሶስት መንገስታትን አይታለች፡፡ ከ2010 ጀምሮ በተለይም የናይል ተፋሰስ ትብብር ስምምነት ማዕቀፍን መፈረም ተከትሎ የመጣውን እና በአባይ ተፋሰስ ሀገራት በተለይ በግብፅ እና በላይኛው ተፋሰስ ሀገራት፤ እንዲሁም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል የተከሰቱትን ውዝግቦች ለመፍታት የሞከረ አንድም መንግስት ግን የለም፡፡ ይልቁንስ ነገሩን ወደማያስፈልግ አተካራ፣ የአለመተማመን እና የጥርጣሬ አዙሪት ሲከቱት ይስተዋላል፡፡ ችግሩን ለመፍታት ሙከራ አደረገ የሚባለው የኤሳም ሻራፍ ጊዚያዊ መንግስትም የላይኛው ተፋሰስ ሀገራትን ከመዞር እና የትብብር ስምምነት ማዕቀፉ እንዲዘገየ ከመጠየቅ የዘለለ ነገር ሳይሰራ በሞሐመድ ሞርሲ መንግስት ተተካ፡፡ በሞሐመድ ሞርሲ ዘመን የተመሰረተው የአንድ ዓመቱ መንግስት የራሱን ህገ-መንግስት ቢያዘጋጅም በዋናነት አክራሪ ኢስላማዊነትን የተላበሰ ነው በሚል፣ ታማሮድ በተባሉ የግብጽ ወጣቶች ንቅናቄ እንዲሁም በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣን ተወገደ፡፡ በሞሐመድ ሞርሲ መንግስት ውዝግቡን ለመፍታት የሚያስችል ጊዜ እና ምክንያት የነበረ ቢሆንም የግብጽ ህግ አውጪ ምክር ቤት ወይም የሹራ ጉባኤ ብዙውን መቀመጫ የተቆጣጠሩት በአክራሪ ኢስላማዊነቱ የሚታወቀው አሁን የታገደው የሙስሊም ወንድማማቾች የፖለቲካ ክንፍ የሆነው የነፃነት እና ፍትሕ ፓርቲ እንዲሁም እጅግ አክራሪ የሚባለው የሰላፊያዎቹ ፓርቲ አል-ኑር የተቆጣጠሩት ነበር፡፡ በዋናነትም እነዚህ ኃይሎች የግድቡን ጉዳይ ከመሰረተ-እምነታቸው እና ከንጽሮተ-ዓለማቸው የተለየ ስላልነበር ኢትዮጵያ የምትገድበውን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አሜሪካዊ እና እስራኤላዊ ቀለም ቀቡት፡፡ ሞርሲም የደም ጠብታችን ወይ የናይል ውሃ ሲሉ እስር ቤት ቀደማቸው፡፡ የሞሐመድ ሞርሲን መንግስት የተካው የሽግግር መንግስት ሲሆን አድሊ መንሱር በሚባሉ የህግ ባለሙያ ፕሬዝዳንትነት የሚመራ መንግስት ነው፡፡ ይህ መንግስት ህገ-መንግስት የማሻሻል/የማርቀቅ ስልጣን የተሰጠው መንግስት ስለሆነ ሃምሳ አባላቶች ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራውን አጠናቅቆ ለፕሬዝዳቱ የህገ መንግስቱን ረቂቅ አስረከበ፡፡ ረቂቅ ህገ-መንግስቱም ለህዝበ-ውሰኔ በ14 እና 15 ጥር 2013 እኤአ ቀርቦ በ97 በመቶ ድጋፍ ተቀባይነት አገኘ ተባለ፡፡ ይሁን እንጅ ይህ ህገ መንግስት በዋናነት በአንቀጽ 44 ላይ ስለ አባይ ውሃ ጉዳይ ያስቀመጠው ድንጋጌ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ መሳቡ አልቀረም፡፡ ለምን?

ናይል/አባይ በግብፅ ህገ-መንግስት

Egypt Constitution drafting committeeሀገራት ህገ-መንግስትን የሚያዘጋጁት በዋናነት በሀገሪቱ ግዛት ውስጥ የበላይ ህግ ሆኖ እንዲሰራ እና የመንግስት ተወካዮች ስልጣን የተገደበ እንዲሆን፣ የዜጎች መብቶች (ሰብዓዊ እና ዴሞክራያዊ) እንዲከበሩ እና እንዲጠበቁ ወዘተ ለማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም የአንዲት ሀገር ህገ-መነግስት ተፈፃሚነቱ በሀገሪቱ ውስጥ ባለ ግዛት እና ግዛት ብቻ ነው ማለት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ ሀገራት በህገ-መንግስታቸው አጠቃላይ ህግ እንደመሆኑ መጠን በዝርዝር ባይሆን የውጭ ግንኙነት ዋና መስመራወቸውን የሚጠቁም ሃሳብ ሊያሰፍሩ ይችላሉ፡፡ ይህን ሲያደርጉ ግን የሌላውን ሀገር ሉዓላዊነት በሚያፈርስ እና ጣልቃ ገብነትን በተመረኮዘ መልኩ አይሆንም፡፡ ቢሞክርም የሚሳካ እና በሌሎች ሀገራት ዘንድ ተቀባይነት የሚያገኝ አይሆንም፡፡ ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ ግብፅን እናገኛለን፡፡ ግብጽ በአዲሱ ረቂቅ ህገ-መንግስቷ በጥቅሉ ማውጫውን ጨምሮ ናይል የሚለው ስም ሰባት ጊዜ ተጥቅሷል፡፡ በመግቢያው ላይ ያረፈው ዓረፍተ ነገር “ግብፅ የናይል ስጦታ ነች እንዲሁም የግብፃውያን ስጦታ ለሰብዓዊነት” ይላል፡፡ ማንም የሚክደው ሐቅ አይደለም ግብፅ የአባይ ስጦታ ለመሆኗ፡፡ አባይ ባይኖር ኖሮ ጥንት ግብፅ ደረቅ በረሐ በሆነ ነበር (አሁን ግን በተገኘ ሳይንሳዊ መረጃ ግብፅ አባይ እንኳን ቢደርቅ ለ500 ዓመታት የሚበቃ የከርሰ ምድር ውሃ ባለቤት ናት)፡፡ የሆነ ሆኖ ግብፅ የአባይ ስጦታ ናት ማለት አባይ የግብፅ ስጦታ ነው ማለት አይደለም፡፡ አባይ/ናይል የሚጋሩት ሀገራት ሁሉ፤ የህዝባቸው ስጦታ ነው፡፡ አባይ/ናይል የሚጋሩት የአስራ አንዱ ሀገራት ገጸ-በረከት ነው፡፡ ይሁን እንጅ ይህን ሐቅ የሚያፈርስ ነገር በግብፅ ረቂቅ ህገ-መንግስት አንቀጽ 44 ሰፍሮ ይገኛል፡፡

አንቀጽ 44 “መንግስት የናይልን ወንዝ ለመከላከል፣ እንዲሁም የግብፅን ታሪካዊ መብት ለማስጠበቅ፣ ጥቅሞቹንም ለማሳደግ እና  ለማረጋገጥ፣ ውሃውንም ከብከነት እና ከብክለት ለመጠበቅ ቁርጠኛ ነው፡፡…. (The state commits to protecting the Nile River, maintaining Egypt’s historic rights thereto, rationalizing and maximizing its benefits, not wasting its water or polluting it…) (በከፊል የተተረጎመ) ይላል፡፡ አሁን እዚህ ላይ ዋና ጉዳዩ ግብፅ በህገ-መንግስቱ ስለ ናይልን ከብከነት እና ከብክለት ለመጠበቅ እንዲሁም ደግሞ ጥቅሙን ከፍ ከማድረጓ አይደለም ችግራችን፡፡ እሱን ቢያደርጉ ምንኛ ባመሰገንናቸው፡፡ ዋናው ጉዳይ ያለው “…የግብፅን ታሪካዊ መብት ለማስጠበቅ…” የሚለው ሀረግ ላይ ነው፡፡ ግብፅ ይህን ስትል ምን ለማለት ፈልጋ ነው? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ ያደርገናል፡፡

ግብፅ አለኝ የምትለው “ታሪካዊ መብት” የሚባል ነገር እንደ ግብፃውያን ትንታኔ በቅኝ ግዛት ዘመን በእንግሊዝ የተፈረመውን የ1929 “ስምምነት” እና እንዲሁም በ1959 በግብፅ እና በሱዳን መካከል የተደረገን ስምምነት የተመረኮዘ ነው፡፡ በነዚህም “ስምምነቶች” መሰረት ግብፅ የተፋሰሱ አምባገነን እንድትሆን ያደረገ ሲሆን ውሃ ከመከፋፈል ባለፈ የላይኛው ተፋሰስ የውሃ ስራዎችን የመቆጣጠር እንዲሁም ስራዎችን የመፍቀድ እና የመከልከል መብት የሚሰጡ ናቸው፡፡ የ1929 “ስምምነት” እንግሊዝ ቅኝ የምትገዛቸውን ሀገራት በመወከል ለራሷ ስትል ከራሷ ጋር የፈረመችውደብዳቤ ልውውጥ ነበር፡፡  ይሁን እንጅ የ1929 የቅኝ ግዛት ውል በመሆኑ እና ነፃ የወጡ ሀገራት አይመለከተንም ሲሉ የሻሩት መሆኑ እንዲሁም ሱዳን ነፃ እንደወጣች እንዲቀየርላት የጠየቀች በመሆኑ ወድቅ የሆነ ያረጃ እና ያፈጀ ጉዳይ ነው፡፡ የ1959 ስምምነትም በግብፅ እና በሱዳን መካከል የተደረገ የሁለትዮሽ ስምምነት ሲሆን የናይልን ዓመታዊ ፍሰት ሙሉበሙሉ በመከፋፈል ለግብፅ 55.5 ቢሊዮን፣ ለሱዳን 18.5 ቢሊዮን እንዲሁም ሰሐራ በረሐ ላይ በተሰራው አስዋ ግድብ እና በተፈጠረው አባካኝ የናስር ሐይቅ አማካኝነት ለሚፈጠር ትነት ከ10 ቢሊዮን በላይ ኪዩቢክ ሜትር ውሃን ይሰጣል፡፡ ለላይኛው የናይል ተፋሰስ ሀገራትም አንዳችም ዓይነት ውሃም ያስቀረ ስምምነት አልነበረም፡፡ ሀገራቱም እንደነበሩ አልጠቆጠሩም፡፡ እንግዲህ ግብፅ ይህን አምባገነናዊ ስርዓት ነው “ታሪካዊ መብቴ” የምትለው፡፡ ኢትዮጵያ በወቅቱ ነፃ መንግስት ስለነበረች ይህ ስምምነት ሲፈረም በይፋ በዓለም መድረክ ተቃውሞዋን ያሰማች ሲሆን፤ ኢትዮጵያን ያላማከለ ማናቸውም የናይል ስምምነት ዋጋ የሌለው እንደሆነ በግርማዊ ቀደማዊ ኃይለሥላ የዙፋን ንግግር እና ካይሮ በሚገኙ ዲፕሎማቶቿ በኩል በ1957 እኤአ አወጀች፡፡ ከዚህ ባሻገረም ማናቸውም ዓይነት ያልተሳተፈችበት ውል የአባይን ውሃ ከመጠቀም እንደማያግዳት ብሎም የዜጎቿን ፍላጎት ለማሟላት ንብረቷ የሆነውን ውሃውን እንደምትጠቀም በግልፅ አሳወቀች፡፡ በወቅቱ በቅኝ ቅዛት የነበሩ ሀገራትም ነፃ በወጡ ማግስት በቅኝ ገዥዎች የተፈረሙ ስምምነቶች እንደማይመለከቷቸው አሳወቁ፡፡ ይህን ነው እንግዲህ ግብፅ “ታሪካዊ መብቴ” የምትለው፡፡

“ታሪካዊ መብት” ከዓለምአቀፍ የውሃ ህግ አንፃር

ዓለምአቀፍ የውሃ ህግ ብለን የምንጠራው እና ሁሉኑም የዓለም ሀገራት በአንድ ያስተሳሰረ አንድ ወጥ ዓለማቀፋዊ ደንብ ወይም ኮንቬንሽን የለም፡፡ ሆኖም ግን በተለያዩ ጊዚያት ዓለምአቀፍ ፍርድ ቤቶች የወሰኗቸው ውሳኔዎች እንዲሁም ደግሞ ወሰን ተሸጋሪ ወንዞችን በሚጋሩ ሀገራት መካከል በተደረጉ ስምምነቶች መሰረት ወደ ልማዳዊ ህግነት ያደጉ መርሆዎች አሉ፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በተለያየ ጊዜ የመጡ የዓለምአቀፍ ህግ ምሁራን በምክኒያታዊነት ያስቀመጧቸው ሐተታዎች እና ትንታኔዎች አንድ የህግ ምንጮች ናቸው፡፡ በጥቅሉ ሲታይ አሁን ባለው የዓለም ስርዓት መሰረት የልማዳዊ ህግ መርህነት ማማ ላይ የወጣው ሚዛናዊ እና ምክንያታዊ የውሃ ግልጋሎት/Equitable and reasonable utilization የተሰኘው መርህ  ነው፡፡ ይህ መርህ በሀገራትም፣ በምሁራንም ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ያስቻለው ዋናው ምክንያት በግርጌም ሆነ በራስጌ ሀገራት ዘንድ የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚያስችል አቅም እንዳለው በመታመኑ ነው፡፡ ለምሳሌ በዳኒዩብ ወንዝ ጋብችኮቮ-ናጊማሮስ ፕሮጀክት ጉዳይ ላይ በሀንጋሪ እና በስሎቫኪያ መካከል በነበረው አለመግባበት የዓለምአቀፉ የፍትሕ ፍርድ ቤት/International Court of Justice ለጉዳዩ ውሳኔ የሰጠው በሚዛናዊ እና ምክንያታዊ የውሃ ግልጋሎት መርህ በመንተራስ ነው፡፡ በአንፃሩ ታሪካዊ መብት የሚባል ዓለምአቀፍ ህግ የሚያውቀው መርህም የህግም ድንጋጌ የለም፡፡ በርግጥ “ታሪካዊ መብት” የሚባለው ሃሳብ “ቀድሞ የመጠቀም መብት፣ የቆየ መብት” ወዘተ በሚሉ ቅጥያ ስሞቹ አንደ አንድ ህልዮት ወይም መሰረተ-እምነት በተለያየ መልኩ ይነሳ ነበር፡፡ ይህም ከወረቀት ያለፈ ነገር የለውም፡፡ በዓለምአቀፍ ህግ መርሆነትም የሚታወቅ ነገር አይደለም፡፡ ለትብብር ስምምነት ማዕቀፉ በተደረጉ ድርድሮችም ሆነ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ በሚደረጉ ውይይቶች ግብፆቹ ይህን “ታሪካዊ መብት” አለን የሚል ፈሊጥ የሚያስገቡት እና የሚያነሱት ከተራ የትምክህተኝነት እና የማንአለብኝነት እብሪት የመነጨ እንጅ እውነታውን ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡

በናይል ተፋሰስ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ

በዓለምአቀፍ ህግ መሰረት ሀገራት ዓለምአቀፍ ጉዳዮችን የሚዳስስ ሀገራዊ ህግን ቢያወጡም ወይንም በህገ-መንግስታቸው ቢጠቅሱም  ሌሎች ሀገራት ይህን የመከታተልም ሆነ የማወቅ ግዴታ የለባቸውም፡፡ የወጣው ህግ ተፈፃሚ የሚሆነው ህገ-መንግስቱን ጨምሮ ህጉን ባወጣው ሀገር ግዛት ውስጥ ብቻ  ነው፡፡ እነዚህ ሀገራትም ያወጡትን ህግ ዓለምአቀፍ ግዴታዎችን ለመሸሽም ይህን ህግ መጥቀስ አይችሉም፡፡ በሌላ አገላለጽ ሌሎች ሀገራትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ዙሪያ ምንጊዜም ዓለምአቀፍ ህግ በብሔራዊ ወይም የሀገር ውስጥ ህግ ላይ የበላይነት አለው፡፡ ከዚህ አንፃር ስናየው ግብፅ ምንም ዓይነት ዓለምአቀፋዊ የህግ መሰረት የሌለውን “ታሪካዊ መበቴ” የሚባል ነገር በህግ-መንግስቷ ማካተቷ አንዳችም ዓይነት የህግ ውጤት የለውም በሌሎች የናይል ተፋሰስ ሀገራት ላይ፡፡ ይሁን እንጅ ይህን ሐረግ ግብፅ በህገ-መንግስቱ ማካተቷ በዋናነት የናይልን ጉዳይ በተመለከቱ የሚደረጉ ውይይቶች ላይ ወትሮም ግትር የሆኑትን ግብፃውያንን ይበልጥ ግትር እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም ዞሮዞሮ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡ ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ያወሳስበዋል፡፡

ሌሎች የላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራትም ሆኑ ኢትዮጵያ አንዳችም የውሃ ጠብታ ያላስቀረን፣ ያልተማከሩበትን፣ ያልተሳተፉበትን፣ የማያውቁትን ብሎም በይፋ በዓለምአቀፍ መድረክ የተቃወሙትን እና ያወገዙትን ያረጃ እና ያፈጀ የቅኝ ግዛት ዘመን የደብዳቤ ልውውጥ የሚቀበሉበት አንዳችም ምክንያት የለም፡፡ ስለሆነም ግብፅ “ታሪካዊ መብቴ” ለምትለው ነገር የሀገራቱ መልስ የሚሆነው በፊትም እንደነበረው ሁሉ “የምትሉትን ነገር አናውቀውም፡፡ አይመለከተንም” የሚል ነው፡፡ ሌላ ምንም መልስ ሊኖር አይችልምና፡፡ ለዚህም እጅጉን የተትረፈረፈ ዓለምአቀፋዊ የህግ መሰረት እና ድጋፍ አላቸው፡፡ ግብፆች ግትር የሆነውን አቋማቸውን ይዘው አሁንም ለውይይት ከመጡ የናይልን ተፋሰስ እንደገና ወደ አለመተማመን እና የጥርጣሬ አዙሪት መክተት ነው፡፡ የላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ይልቁን አሁን መስራት ያለበቻው የናይል ተፋሰስ ትብብር ስምምነት ማዕቀፍ (CFA) የፈረሙ ሀገራት እንዲያጸድቁ እንዲሁም ያልፈረሙትም ፈርመው እንዲያጸድቁ ማድረጉ ላይ ነው፡፡ ግብፅ በዚህ ህግ መንግስት ረቂቋ ለማለት የፈለገችው የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት ምንም አያመጡም፣ የቅኝ ግዛት ጠባሳውን ታቅፈው ይኖራሉ ነው፡፡ እውነታው ግን በግንቦት 14 ቀን 2010 እኤአ በኢንቴቤ ዩጋንዳ የተፈረመው ስምምነት የሁሉን የተፋሰሱን ሀገራት መብት ባስጠበቀ መልኩ የተፈረመ እና ያለፈውን ኢ-ፍትሀዊነት እና አምባገነናዊነት የሚንድ በመሆኑ መልሱ እዛ ላይ አለ፡፡

ምን ይፈጠር ይሆን….

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ያቀረባቸውን ምክረ-ሃሳቦች ለመተግበር ስለሚኖረው አካሄድ በግብጽ፣ በሱዳን እና በኢትጵያ መካከል በሶስት ዙር የተካሄደው ውይይት በግብፅ አምቢተኝነት እና አፍራሽ እንቅስቃሴዎች ዳር ሊደርስ አልቻለም፡፡ ወደፊት ውይይቱ ይቀጥላል አይቀጥልም የሚለውም ጉዳይ ገና እልባት ያገኘ ጉዳይ አይደለም፡፡ ግብፅ ከሶስተኛው ዙር የካርቱም ውይይት (ከጥር 4-5 2013 እኤአ) በኋላ አንድም በግብፅ ሁለትም በመካከለኛው ምስራቅ የመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት አፍራሽ የሆኑ እና ኢትዮጵያን ለማሳጣት የሚሞክሩ ስሞታዎችን አቅርባለች፡፡ እውነታው ለውይይቶቹ መደናቀፍ ያለ አጀንዳው ጉዳይ እያነሱ እና የዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድኑ ካቀረበው ምክረ-ሃሳብ ጋር የማይሄድ ኮተቶችን እያመጡ ያስተጓጎሉት እነሱው ራሳቸው የግብፅ ተወያዮች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ግብፅ የምትለውን ነገር የማትቀበል ከሆነ ግብፃውያን ወደ ውይይት እንደማይመለሱ አስታውቀዋል፡፡ አሁን ደግሞ በቅርቡ ግብፅ ካሊድ ዋሲፍ የተባሉ የመስኖ እና ውሃ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አል-ሞኒተር በተሰኘ የመካከለኛው ምስራቅ የበይነ-መረብ የዜና ምንጭ አማካኝነት ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መነግስታት እንወስዳለን የሚል ነገር አስነብበዋል፡፡ ይሁን እንጅ ወደ ተባበሩት መንግስታት እንወስደዋለን የሚለው ፉከራ የግድቡን ግንባታ ለማጓተት የሚወጠን ሴራ እንጅ በዚያውም መድረክ ቢሆን እንደሚሸነፉ ያውቁታል፡፡

ግብፅ ዓለምአቀፍ የገንዘብ ተቋማትን እና አጋሮችን በማስቸገር ለኢትዮጵያ ገንዘብ አትስጡ የሚል ውትወታዋም የሚያተርፍላት የኢትዮጵያውያንን ቂም ብቻ ነው፡፡ ግድቡን ከመገደብ የሚያስቆም አንዳችም ኃይልም እንደሌለ ያውቁታል፡፡ ዞሮዞሮ ያለውን ውዝግብ ለመፍታት ትክክለኛው መንገድ በውይይት እና በመልካም ጉርብትና መርህ ተመርኩዞ የጋራ የሆነውን ሀብት ለጋራ ማልማት ነው፡፡ እንደዚህ ጸኃፊ እይታ ግብፆች ሁሌም እንደሚያደርጉት ሄድን አንመጣም ይላሉ፡፡ ነገር ግን ወደ ውይይቱ መድረክ መምጣታቸው አይቀርም፡፡ ይመጣሉ፡፡ ሲመጡ ግን ሌላ ምን ነገር ይዘው ይመጡ ይሆን ነው ጥያቄው፡፡ የሆነ ሆኖ ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት እንዳደረገችው አሁንም ሳትዘናጋ ግድቡንም መገደብ ውይይቱንም ማስኬድ ብቸኛ አካሄድ ነው፡፡ ግድቡን ውይይቱ እስኪያልቅ ወዘተ ይቁም የሚባለው ነገር ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም-ህዝብን አስይዞ እንደመወያየት ነውና፡፡ ይህም የሚታሰብ አይሆንም፡፡ ለግብጽ አሁንም ለውይይት በሩ ክፍት ነው፡፡ ውይይቱ ካልጣማት ግን … “ከሰው ላይ ሰው፣ በታች ያለ ይባሰው” ይሆናል ነገሩ፡፡

ይህ ጽሁፍ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 200 ጥር 17 ቀን 2006 ዓ.ም. ታትሞ የወጣ ነው፡፡

Advertisements

One thought on “የግብጽ ረቂቅ ህገ-መንግስት እና የአባይ ውሃ ጉዳይ

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s