አሉላ አባ ነጋ፡ የጉራዕው አንበሳ ከ138 ዓመታት በኋላ

ዘሪሁን አበበ ይግዛው

ምክንያተ-ጽህፈት

hidaseእንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በመጋቢት 7 ቀን 2014 የአቢሲኒያ ፍላይት ባለቤት ካፒቴን ሶሎሞን በሚያበሯት ሚጢጢ የሰማይ ታክሲ-አስር ሰው የምትይዝ ትንሽ አውሮፕላን ውስጥ የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስቴር የተከበሩ አቶ አለማየሁ ተገኑን፣ አመብሳደሮችን እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባለሙያዎች ቡድን እና ጋዜጠኞችን ይዛ አቅጣጫዋን ወደ ምዕራብ ኢትዮጵያ በማድረግ ወደ ጉባ ወረዳ ቤንሻንጉል-ጉሙዝ ክልል አቀናች፡፡ የጉዞው ዓላማም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የደረሰበትን ሁኔታ ለማየት ነው፡፡ እንደ ዕድል ሆኖ ምስጋና ለክቡር ሚኒስትር አቶ አለማየሁ ተገኑ እና ለአቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ (በውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጅ ሚኒስቴር የወሰን እና ወሰን ተሸጋሪ ወንዞች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር) ይሁን እና በዚች ትንሽ አውሮፕላን ውስጥ ሆኜ ቁልቁል አባይ ደንበር ሊሻገር ሲጣደፍ ሳየው ንዴት ውስጤን አቃጠለው፡፡ ተመልሼ ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ሳስብ ይህ ወንዝ ለሀገሩ ሊቆም ነው ብዮ ተጽናናሁ፡፡ ወዲያውም የበውቀቱ ስዩምን

ከተመኙ ላይቀር ወንዝነት መመኘት

አገርን ሳይለቁ ሌላ ሀገር መገኘት፡፡

የምትል ስንኝ ለራሴው አስተውሼ ፈገግ አልኩኝ በውስጤ፡፡ ግን አሁንም አሁንም ውስጤን ቁጭት አልለቀቀውም ነበር፡፡ አንዳች ስሜትም ውስጤን ይኮረኩረው ነበር፡፡ በመሐል ግን እንደ ድንገት ዶ/ር ጌታቸው አሰፋ በአዲስ ጉዳይ መጽሐት “የ ‘ጉ’ ቤት ለግብፆች” ብሎ የከተበው መጣጥፍ ትዝ አለኝ፡፡ ጉንደት—- ጉራዕ— ጉባ—- አልኩ በለሆሳስ ቃላቱ እና ድርጊቶቹ ተከታትለው በዓይነ ህሊናየ እየተመላለሱ፡፡ ያለ ነገር አልነበረም ትዝ ያሉኝ፡፡ አንዳች የቀን መገጣጠም ስላላቸው እንጅ፡፡ ልክ በዚህች ቀን የዛሬ 138 ዓመት ነበር ራስ አሉላ አባ ነጋ በጉራዕ ታሪክ የሰራው፡፡ ለዛች ታሪካዊ ቀን መታሰቢያ ትሆን ዘንድ እና እንዲሁም ከመጋቢት 7 ቀን እስከ መጋቢት 9 ቀን 1876 የተደረገውን የጉራዕ ጦርነት ለመዘከር የሚከተለውን ለማለት ወደድኩ፡፡ “በጉባ ሰማይ ስር፡ አጭር የጉዞ ማስታወሻ” የምትል አጭር ማስታወሻ በቅርቡ አስነብባለሁ፡፡ እስከዛ ግን እንሆ በረከት… አሉላ አባ ነጋ ወዲ ቁቢ….

ሞሐመድ ዓሊ፣ ኬዲቭ እስማኤል ፓሻ እና ኢትዮጵያ

በ1805 (ሁሉም ዓመቶች እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ናቸው) የኦቶማን ቱርክ የግብፅ አስተዳዳሪ ሆኖ የተሾመው አልባኒያዊው ሙሐመድ ዓሊ ወደ አፍሪካ መምጣት ለብዙ ክስተቶች ምክንያት ሆኗል፡፡ በወቅቱ የኦቶማን ቱረክ ኢምፓየርን መዳከም ያስተዋለው ሙሀመድ ዓሊ ፓሻ የራሱን ኢምፓየር ከግብፅ ወደ ደቡብ አና ወደ ሰሜን እስከ መካከለኛው ምስራቅ ለመዘርጋት ዕቅድ ነበረው፡፡ ይሁን እንጅ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሊያደርግ ያሰበው ዘመቻ የተገታው በወቅቱ አካባቢውን ይቃኙ በነበሩት በእንግሊዝ እና በፈረንሳይ ኃይሎች ነበር፡፡ ሆኖም በደቡብ በኩል ከልካይ ያላገኘው አልባኒያዊ በ1821 ሰሜን ሱዳንን ተቆጣጠር፡፡ ሲቀጥልም ዓይኑን ኢትዮጵያ ላይ ጣለ፡፡ ከ1805 እስከ 1849 ስልጣን ላይ የቆየው ሙሐመድ ዓሊ በዋናነት የተሳካለት ግብፅ ራሷን የቻለች እና ከኦቶማን ቱርኮች ነፃ የሆነች ሀገር መመስረቱ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል የኦቶማን ግዛቶች የነበሩ የቀይ ባህር እና የህንድ ውቅያኖስ አዋሳኝ ጠረፎችንም በግብፅ ስር ለማድረግ ጥሯል፡፡ የግብፅ ሱዳንን መያዝ ተከትሎም ከኢትዮጵያ ጋር በዋድ ካልታቡ፣ በዋልቃይት እና በጠገዴ አካባቢ ከተደረጉ ጦርነቶች ነበሩ፡፡ ዋና እና የከረሩ ጦርነቶች የተካሄዱት ግን የሙሐመድ ዓሊ የልጅ ልጅ ኬዲቭ እስማኤል ፓሻ (1863-1879) ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ ነበር፡፡

የአያቱን የመስፋፋት ሃሳብ ለማሳካት ደፋ ቀና ብሎ፤ ብዙ ደክሞ እና በአሜሪካውያን እና በአውሮፓውያን በአማካሪዎች እና በቅጥረኛ ወታደሮች ታጅቦ ኢትዮጵያን ለመውረር ቆርጦ የነበረው ኬዲቭ ኢስማኤል ፓሻ ዓላማው ከግዛት ማስፋፋት ባለፈ ነበር፡፡ ወንድምነህ ጥላሁን በ1979 ባሳተሙት መጽሐፍ እንዳሉት ወረራው በዋናነት በጣና ሐይቅ እና በጥቁር አባይ ያነጣጠረው የግብፅ ኢምፔሪያሊስታዊ ፍላጎት ውጤት ነበር፡፡ እንዲሁም በተመሳሳይ መልኩ እንዲሁ የኬዲቭ እስማኤል ታሪክ ጸኃፊ እንደገለጸው እና በስቨን ሩቢንሰን (1976) እንደተጠቀሰው “የኬዲቩን ቅኝ ግዛት ስራ በአንድ አገላለጽ ማጠቃለል ይቻላል፤ ሁሉንም የናይል ተፋሰስ መሬት በሀገሩ ቁጥጥር ስር በማድረግ የናይልን ወንዝ ግብፃዊ ወንዝ ማድረግ ይፈልግ ነበር፡፡” ይህንን ለማሳካትም ተደጋጋሚ እና ያላቋረጡ የወረራ ሙከራዎችን አድርጓል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ሙከራዎች ከሙከራት አልዘለሉም፡፡ በዋናነት የሚጠቀሱት ሁለት ዓበይት ጦርነቶች ደግሞ የ1875 የጉንደት እና የ1876 የጉራዕ ጦርነቶች ናቸው፡፡ በሁለቱም ጦርነቶች ወራሪዎቹ ግብፆች እና አጋዥ ቅጥረኛ ወታደሮች እና አማካሪ ጄኔራሎች ሽንፈትን ተጎንጭተው ተመልሰዋል፡፡ ድልም ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን ሆነ፡፡ ከአነዚህ ሁሉ ድሎች በስተጀርባ ደግሞ የአንድ ሰው ስም ሁሌም በጉልህ ይነሳል፡፡ አሉላ አባ ነጋ!!

የአሉላ ወዲ ቁቢ አነሳስ

ራስ አሉላ በ1847 በተምቤን ዙቁሊ ሚካኤል እንደተወለዱ ማሞ ውድነህ በ1987 የዶጋሊ ጦርነትን 100ኛ ዓመት በማስመልከት በተዘጋጀው ልዩ የመታሰቢያ ታሪካዊ ጉባዔ ላይ ባቀረቡት ጽሁፍ ይገልፃሉ፡፡ ደራሲ ማሞ ውድነህ እንደሚሉት የራስ አሉላ አባት እንግዳ ቁቢ አራት ልጆቻቸውን ራስን እና ሀገርን መከላከል እንዴት መማር እንደሚቻል ያስተምሩ ነበር፡፡ አሉላ ግን ከሁሉም ይልቁ ነበር፡፡ በዙቂሊ ሚካኤልም ከመምህር ወልደጊዮርጊስ ይማሩ እንደነበረ ማሞ ውድነህ አብራርተዋል፡፡ አሉላ ወዲ ቁቢ የጉልምስና ስራውን በአጼ ዮሐንስ አጎት በራ አርአያ ደምሱ ቤት አሽከር በመሆን እንደጀመሩ ፕሮፌሰር ንጉሴ አየለ “Ras Alula and Ethiopia`s Struggle Against Expansionism and Colonialism: 1872-1897” በተሰኘ መጣጥፋቸው ገልጸዋል፡፡ እንደ ፕሮፌሰረ ንጉሴ ገለፃ ራስ አሉላ በስተኋላ ወደ ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ (ኋላ አፄ ዮሐንስ 4ተኛ) ቤት ከተዛወሩ በኋላ ሹመትን በሹመት በመደረብ ወደፊት ገሰገሱ፡፡ በመጀመሪያ እልፍኝ አስከልካይ ቀጥሎም አጋፋሪነትን ተሾሙ፡፡ በ1873 ደጃዝማች ካሳ ንጉሰ ነገስት አጼ ዮሐንስ አራተኛ ሲባሉ አሉላ የሻለቅነትን ማዕረግ የንጉሱ ሊጋባነት ማዕረግን ደርበው ያዙ፡፡

አሉላ ወዲ ቁቢ ሁለንተናቸው ስሁል፣ ንቁ እና አርቆ አሳቢ እንደነበሩ ብዙ ጸሐፊዎች፣በጦር ሜዳ ውሎ የሚያውቋቸው፣ በዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሚውቋቸው ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡ ዛሬ ላይ ሆነው ነገን የሚመረምሩ ከራስ በላይ ሀገርን የሚስቀድሙ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ነበሩ አሉላ ወዲ ቁቢ፡፡ ፕሮፌሰር መርዕድ ወልደ አረጋይ “Alula, Dogali and Ethiopian Unity” በሚል ጽሁፋቸው ከአሳዛኙ የአፄ ቴውድሮስ የመቅድላ ፍፃሜ በፊትም ሆነ በኋላ አፄ ቴውድሮስን የመሰለ አንድ ሰው ቢኖር አሉላ አባ ነጋ ብቻ ናቸው፡፡ እንደ ፕሮፌሰር መርዕድ ገላፃ ከሆነ ራ አሉላ ከአጼ ቴውድሮስ ጋር በተክለ ሰውነት መመሳሰል ባለፈ በሰብዕና እና በአመለካከት እንዲሁም በአርቆ አሰተዋይነት እና በመንፈሳዊ ልዕልና ይመሳሰላሉ፡፡ ግብርን ለሀገር ጥንካሬ ከማዋል ባለፈ አንድ የጦር መሪከተራው ወታደር የተለየ መብላት እና መልበስ እንደሌለበትም ሁሉቱ የኢትዮጵያ ጅግኖች ተመሳስሎ እንደሆነ ፕሮፌሰር መርዕድ ያስረዳሉ፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ማሞ ውድነህ “The Life and Works of Alula Aba Nega” በሚለው መጣጥፋቸው እንደሚያስረዱት አሉላ ወዲ ቁቢ በ1847 እንደመወለዳቸው ስለ አፄ ቴውድሮስ ጀግንነት እና ትልቅነት እየሰሙ ማደጋቸውን ያብራራሉ፡፡

አሉላ ወዲ ቁቢ ከነበራቸው የቶር ብልሀት እና እንዲሁም ደግሞ የተዋጣለት ዲፕሎማት መሆን የተነሳ በአፄ ዮሐንስ ፊት ሞገስ እና ክብር ነበራቸው፡፡ ለዛም ነው ከአሽከርነት እስከ ራስነት ሹመት የደረሱት፡፡ በታሪክ ዘመናቸው በዋናነት ለአፄ ዮሐንስ የቀኝ እጅ በመሆን በወቅቱ ንጉሱን ከገጠማቸው የስልጣን ሽኩቻ በተለይ ከጎጃም እና ከሸዋ ከማደላደል ባሻገር ከሶስት ዋና ዋና የኢትዮጵያ የወቅቱ ጠላቶች ጋር ተዋግተዋል፡፡ በዋናነትም ከህዳር 16 ቀን 1875 ከተደረገው የጉንደት ጦርነት እስከ መጋት 1 ቀን 1896 እስከተደረገው የአድዋ ጦርነት ድረስ ራስ አሉላ አባ ነጋ አስራ ሁለት ጦርነቶችን ከውጭ ወራሪ ኃይሎች ጋር የተዋጉ ሲሆን በዋናነትም ከኦቶማን ግብጽ ተስፋፊዎች፣ ከማህዲስት የድርቡሽ ወራሪዎች እና ከጣሊያን ቅኝ ገዥዎች ጋር ያደረጓቸው ናቸው፡፡

ራስ አሉላ አባ ነጋ (የጉራዕው አንበሳ) እና የጉራዕ ጦርነት

Alula Aba Negaከላይ ለማየት እንደሞከርነው ግብፅ ኢትዮጵያን ለመያዝ በወቅቱ የተነሳችበት አበይት ምክንያት አባይን ከነ ምንጩ የግብፅ ወንዝ ለማድረግ ከነበራት ቅዠት የመነጨ ነበር፡፡ ግብፅ ኢትዮጵያን ለመውረር ስታስብ በዋናነት ከሶስት አቅጣጫዎች በመቦትረፍ ነበር፡፡ አንደኛው በሐረር በኩል፣ ሁለተኛው በሰሜን በምፅዋ በኩል ወደ ደጋው በመዝለቅ ሲሆን ሶስተኛው ደግሞ በአዳል ወይም አፋር በኩል በመግባት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ቀዠታቸው ቅዠት ሆነ ነበር የቀረው፡፡ ከሁሉም እጅግ ወሳኝ የሚባሉት ጢርነቶች በተከታታይ ዓመታት የተደረጉት የ1875ቱ ጉንደት እና የ1876 ጉራዕ ጦርነቶች ናቸው፡፡ በ1875 ህዳር ወር በ ጄኔራል አሬንድሩፕ የሚመራው የግብፅ ጦር እነ አራኬል ቤይ፣ ሩስተም ቤይ እና በመሳሰሉት ቅጥረኞች የተመራው ከ3000 በላይ የሆነ የግብፅ ጦር ጉንደት ላይ ለማጥቃትም ለመከላከልም እንዲመቸው ሆኖ  መሸገ፡፡ በኢትዮጵያ በኩል አፄ ዮሐንስ አራተኛ በሁለት ሳንት ውስጥ ከ20000 እስከ 30000 የሚጠጋ ሰራዊታቸውን በማሰባሰብ በእነ ራስ አራያ፣ ራስ ባርያ ገብር፣ ባሻ ገብረማርያም፣ ደጃዝማች ሀጎስ፣ ደጃዝማች ወልደ ሚካኤል፣ ደጃዝማች ተሰማን እንዲሁም ሻለቃ አሉላን አስከትለው ወደ ጉንደት አቀኑ፡፡ ራስ አሉላ በዚህ ወቅት ነበር ጅግንነታቸው የታየው እና ከሌሎቹም ልቀው መውጣታቸው የተስተዋለው፡፡ በድንገተኛ የማጥቃት ስልት በመከተል ኢትዮጵያውያን አርበኞች 30 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በአሬንድሩፕ የሚመራው ወደ 800 የሚጠጋ ሰው እንደ ቅጠል ረገፈ፡፡ “The Survival of Ethiopian Independence” በተሰኘ ድንቅ መፅሐፋቸው ስቨን ሩቢንሰን እንደከተቡት ይህ ሲሆን በኢትዮጵያ በኩል 31 አርበኞች ሲሰው 51 ብቻ ነበር የቆሰሉት፡፡ ከጥቂት ሰዓተት በኋላም የተቀሩትን 1300 የግብፅ ወታደሮች በመክበብ ከአንድ ሰዓት ተኩል ባልበለጠ ከበድ ያለ ውጊያ ኢትዮጵያውያን አረበኞች ዶግ አመድ አደረጓቸው፡፡ በኢትዮጵያ በኩልም 521 ሰው ሲሞት ወደ 355 ቆሰለ፡፡ በእነ ሻለቃ ዴኒሰን ይመራ የነበረው እና ለጉንደት ተዋጊ ወታደሮች ደጀን ለመሆን አዲ ቋላ መሽጎ የነበረው የግብፅ ሰራዊትም ፈረጠጠ፡፡ በአንፃሩ ከምፅዋ በኩል ወደ ስድስት መቶ የሚጠጉ ወታደሮችን አስከትሎ በአዳል/አፋር በኩል ወደ ኢትዮጵያ የዘለቀው እና በስዊዛዊው ቅጥረኛ ጆሀን አልበርት ወርነር ሙንዚንገር ፓሻ የሚመራው ሰራዊት በሞሐመድ አንፍሬ የተዘጋጀለትን ድግስ አጣጣመ፡፡ መሪውን ወርነር ሙንዚንገር ፓሻን ጨምሮ አንድም ወሬ ነጋሪ ሳይተርፍ የግብፅ ወራሪ ኃይል በአፋር አርበኞች ተረፈረፈ፡፡

ሽንፈትን እንደ ውሃ ደጋግሞ የተጎነጨው የግብፅ የኬዲቭ እስማኤል ፓሻ አስተዳደር ግን ሽንፈቱ ሊዋጥለት አልተቻለውም፡፡ እናም ሌላ መሰናዶ እና ጉዞ፤ ሌላ ጦርነት እና ፍልሚያ አሰኘው፡፡ የሚቀጥለውን ፍልሚያም ለማሸነፍ ቆርጦ ተነሳ፡፡ ከጉንደት ከነበረው አሰላለፍ በበለጠ በአዲስ አደረጃጀት እና ብዙ ቁጥር ያለው ወታደራዊ ኃይል በማነቃነቅ፣ አዳዲስ ቅጥረኞችን በማስመጣት (በተለይ ከአሜሪካ የርስ በርስ ጦርነት መሪ ተሰላፊ የነበሩ ቅጥረኞችን) እንዲሁም አዳዲስ የቶር መሣሪያዎችን በመታጠቅ ኢትዮጵያን ለመውጋት እና ለማንበርከክ ቆርጦ ተነሳ፡፡ ይህን በማድረግም አያቱ ሙሐመድ ዓሊ የተመኘውን አባይን ከእነ ምንጩ የመያዝ ቅዠት እውን ለማድረግ ቆረጠ፡፡

የወቅቱ 500 000 ፓውንድ ሰተርሊንግ የተመደበለት እና ወደ 20000 የሚጠጉ ግብፃውያንን እና ቅጥረኞችን የያዘው የግብፅ ጦር ከአስመራ 40 ኪሎ ሜትር በስተደቡብ በምተገኘው ጉራዕ ሁለት ምሽጎችን መስርቶ ለ,እንደ ጉንደት ሁሉ ለማጥቃትም ለመከላከልም እንዲመቸው ሆኖ መሸገ፡፡ በወቅቱ የግብፅ ጦር የወቅቱን ዘመናዊ የሚባል የጦር መሣሪያ የታጠቀ ሲሆን በዋናነትም ረሚንገቶን እና ክሩፕ የተሰኙ ጠብመንጃዎችን፣ አርባ መድፎችን እና 10 ሮኬት ማስወንጨፊያዎችን የያዘ ነበር፡፡ ሊጋባ አሉላ መረብን እንደተሸገረ የኢትዮጵያን ሰራዊት በአምስት በመክፈል እና ግብፆቹን በማጨነቅ ሜዳ ላይ ወጥተው እንዲዋጉ አስገደዳቸው ይላሉ ማሞ ውድነህ በመጣጥፋቸው፡፡ የጉራዕ ጦርነት የተጀመረው ልክ የዛሬ 138 ዓመት በመጋቢት 7 ቀን 1876 ነበር፡፡ በዚህ ዕለት ወደ ሰባት ባታሊዮን የሆነው የግብፅ ጦር ውስጥ ከ5000 እስከ 6000 የሚጠጋ ሰራዊት መካከል ምንም ሳይሆን የተረፈው ከ400 እስከ 600 የሚጠጋ ሰው ብቻ እንደነበረ ስቨን ሩቢንሰን በመጽሐፋቸው ይገልፃሉ፡፡

ምስጋና ለአሉላ አባ ነጋ እንግዳ ይሁን እና በተከተሉት የቶር ስልት መሰረት ከ3600 በላይ ግብፃውያን ሲሞቱ ይዘዋቸው የነበሩ መድፎች እና እጅግ ቁጥራቸው የበዛ በሺዎች የሚቆጠሩ ጠብመንጃ የጦር መሣሪዎች በኢትዮጵያውያን እጅ ወደቁ፡፡ ጦርነቱ በመጋቢት 8 እና 9 ቀጥሎ የዋለ ሲሆን በዋናነት በሁለቱ ቀናት ግብፃውያን ከምሽጋቸው ሆነው ባደረሱት ጥቃት ከመጀመሪያው ቀን ጋር ሲነፃፃር በኢትዮጵያ በኩል ከፍ ያለ ሞት ተመዘገበ፡፡ በጥቅሉ ግን  ወደ 4000 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን በሶስቱ ቀናት ውጊያዎች አጥታለች፡፡

የጉራዕ ውጊያ ለግብፃውያን እጅጉን አስተማሪ የሆነ ጦርነት ነበር፡፡ ደጋግመው ከጉራዕ በፊት የሞከሯቸው ጦርነቶች በሰው ቁጥር ማነሰ የመጣ የመሰላቸው ግብፃውያን መሪዎች እጅግ ብዙ የሚባል ቁጥር የነበረው እና በአውሮፓውያን፣ አሜሪካውያን እና ቱርካውያን ምክር እየተደገፈ ከዘመናዊ የጦር መሣሪያ ጋር የዘመተ ጦራቸው ድባቅ እንደተመታ አስተውለዋል፡፡ ኢትዮጵያን የመያዝ ጉራቸውም የጉራዕ ጦርነት ላይ አሉላ በመራው ጦር ጉራ ሆኖ ቀርቷል፡፡ የኢትዮጵያም ሉአላዊነት በቆራጥ ጀግኖች ልጆቿ ተከበረ፡፡ ይህን ሁሉ እያብሰለሰልኩ ነበር ዓበይን ቁልቁል ወደ ደንበር በጉባ ሲጣደፍ እያየሁ ጉራዕንም እያስታወስኩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አውረፕላን ማረፊያ ሚጢጢዋ የካፒቴን ሶሎሞን አውሮፕላን መሬት ነካች፡፡ እኔም መሬት ያያዘውን እና በጥድፊያ ቁመቱ እየተመነደገ ያለውን ታላቁን ግድብ በዓይኔ በብረቱ ለማየት እየተጣደፍኩ ወደ ተዘጋጀልኝ መኪና አመራሁ…  ስለ አሉላ አባ ነጋ ብዙ የምለውና የምጽፈው አለ… በሌላ ጽሁፍ እንገናኝ… ክብር ሞገስ በጉንደት፣ በጉራዕ ለተሰው የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን አርበኞች…

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s